“ኹለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በቅርቡ ይጀመራል” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አክለውም የግድቡ ግንባታ 80 በመቶ መጠናቀቁን ያነሱ ሲሆን፣ እስካሁን ለግድቡ ግንባታ 15 ቢሊዮን ብር በአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መዋጣቱን አስታውቀዋል።
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳሚ ሹክሪ የግድቡ ኹለተኛ ዙር ሙሌት በግብጽ ላይ ጉዳት እንደማያስከትል መናገራቸውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ሳሚ ሹክሪ ይህን ያሉት “እንደማይጎዳቸው ስለተረዱ ነው” ብለዋል አምባሳደር ዲና።
በግድቡ ዙሪያ ከስምምነት በፊት መሙላት አትችሉም፤ ምርጫውን አታካሂዱም፤ የሚሉ የአሜሪካ ሴናተሮች ጫና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ እና ህወሓትን በሚደግፉ ቡድኖች የሚደረጉ ተገቢ ያልሆኑ ጫናዎች እንዳሉ አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ከምርጫ ጋር በተያያዘ “ምርጫ አታካሂዱ አንልም፤ የአሜሪካ መንግሥትም ለዚህ አላከኝም” ማለታቸውንም አስታውሰዋል። ይሁንና ግን “ከህወሓት ጋር ጭምር ተነጋገሩ የሚል” ሀሳብ ማንሳታቸውን አምበሳደር ዲና ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታም 36 የውጭ አገራት እና የአገር ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ምርጫውን ለመታዘብ እየተዘጋጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013


