የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን የሚዲያ ጥቃት ጥቆማና ቅሬታን የሚቀበልበት የስልክ ማዕከል አቋቋመ

0
1159

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሚዲያዎች ላይ የሚታዩ ጥቃቶችንና ቅሬታዎችን የሚቀበልበት የስልክ ማዕከል ማቋቋሙን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። ባለሥልጣኑ ያቋቋመው የስልክ ጥሪ ማዕከል ከዚህ በፊት ያልነበረ እንደሆነ ተመላክቷል። የባለሥልጣኑ የስልክ ጥሪ ማዕከል ከዚህ በፊት ያልነበረ እና ለማቋቋምም ጥረት የተደረገ ቢሆንም ሳይሳካ መቆየቱን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ኢንድሪስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ በሚዲያዎች ላይ ከሕዝብና ከግለሰብ የሚቀርቡ የጥቃት ጥቆማዎችንና ቅሬታቸዎችን የሚቀበልበት የስልክ ማዕከል እስካሁን ያልነበረው መሆኑ ትልቅ ክፍተት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ባለሥልጣኑ አዲስ ያቋቋመው የጥቆማና ቅሬታ መቀበያ የስልክ ማዕከል በሚቀጥለው ሳምንት ሥራ እንደሚጀምር ዋና ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የስልክ ጥሪ ማዕከሉ የተቋቋመበት ዋና አላማ በመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞች እና ማስታወቂያዎች ላይ የሕብረተሰቡን ቅሬታና ጥቆማ ለመቀበል መሆኑ ተመላክቷል። ማዕከሉን ለማቋቋም ቀደም ብሎ ሥራ የተጀመረ ቢሆንም፣ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ምክንያት ሥራው ተቋርጦ መቆየቱ ተጠቁሟል።

በበጀት እጥረት ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል የተባለው የባለሥልጣኑ የቅሬታና ጥቆማ መቀበያ የስልክ ማዕከል፣ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሥራው መጠናቀቁን መሐመድ አብራርተዋል። ለስልክ ጥሪ ማዕከሉ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘለትም መሐመድ አክለው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ የ2013 የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጻም ሪፖርቱን ግንቦት 11/2013 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ፣ ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት፣ ለበጀት ዓመቱ ከተፈቀደለት 67 ሚሊዮን 800 ሺሕ ብር በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተጠቀመው 18 ሚሊዮን 18 ሺህ ብር ብቻ በመሆኑ የበጀት እጥረትን እንደምክንያት ማንሳት እንደማይቻል ምክር ቤቱ ገልጿል።

ምክር ቤቱ የባለሥልጣኑን የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸመ በገመገመበት ወቅት፣ የባለሥልጣኑ በጀት አጠቃቀም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጾ፣ የስልክ ማዕከል የማቋቋም ሥራ በበጀት እጥረት ቆሟል መባሉ አሳማኝ አለመሆኑን ጠቁሟል።

በሌላ በኩል፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከዚህ በፊት በቀን ስምንት ስዓት ይከታተል የነበረውን የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎችን፣ በአሁኑ ጊዜ በማሳደግ 24 ስዓት የሚሰሩትን ሥራ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል። የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎች ክትትል በሳምንት ሰባት ቀን እሁድና ቅዳሜን ጨምሮ የ24 ስዓት ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ተመላክቷል።

ከዚህ በፊት የነበረው የባለሥልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎች ክትትል በመንግሥት የሥራ ስዓት ከሰኞ እስከ አርብ በቀን ስምንት ስዓት ብቻ የነበረ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰው፣ የክትትል ሪፖርትም የሚገመገመው በሳምንት መሆኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ ግን የሁሉንም መገናኛ ብዙኃን ሥራዎች በየዕለቱ እየገመገመ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ዳይሬክተሩ ለምክር ቤቱ ጠቁመዋል።

በዚሁ መሰረት የቀን ተቀን ሪፖርቶችን በማጠናከር፣ በሳምንት አጠቃላይ አዝማሚያው እየተተነተነና በወር አጠቃላይ ጥልቅ ትንተና እየተደረገ ባለሥልጣኑ ፈጣን ግብረ መልስና ችግሮችን የማስተካከል ሥራ እየሰራ ነው ተብሏል። ባለሥልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን 150 ችግሮችን በመለየት ችግሮቹ እንዲታረሙ አድርጌያለሁ ብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here