የኹሉም ነገር መሰረትና የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሠላምና ሠላም ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ። ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ግንቦት 18/2013 ተጀምሯል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ የጉባኤውን መከፈት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የኹሉም ነገር መሠረትና የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሠላምና ሠላም ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ስለሆነም መንግሥትም ሆነ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አስፈላጊው ነገር ኹሉ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አንስተዋል።
ዋስትና ያለው ሠላም በአገሪቱ ሊረጋገጥ የሚችለው ኹሉም ባለ ድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስበው መወያየት ፣ መግባባትና አገራዊ ሥምምነት ላይ መድረስ ሲችሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ጉባኤው በጸሎት፣ በማስታረቅ፣ በቁሳቁስና በመጠለያ እንዲሁም በምግብና መጠጥ ድጋፍ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በቅዱስ ሲኖዶሱ ዓመታዊ ምልዓተ ጉበኤ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሰቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ የኹሉም አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ተሳትፈዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013


