የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ለታሪኩ ጋንኪስ /ዲሽታ ጊና/ የ100 ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ሁሉም ወረዳዎች ከ10 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር ሽልማት አበርክተዋል፡፡ የጂንካ ከተማ አስተዳደር የ470 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ካርታ አስረክቧል።
የድምጻዊው አድናቂዎችና ደጋፊዎች ደግሞ የዓይነትና የገንዘብ ሽልማት ሲሰጡ፣ የደቡብ ኦሞ ሕዝቦች ልማት ማኀበርና የአሪ ሕዝቦች ልማት ማኀበር የ8 እና የ30 ሺሕ ብር ሽልማት አበርክተዋል።
የናሳ እርሻ ልማት አግሮ ኢንዱስትሪ የግል ካምፓኒ ባለቤት ገበየሁ ምናሉ 40 ሺሕ ብር ሸልመውታል።
ለታሪኩ ጋንኪስ /ዲሽታ ጊና/ የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደርን ጨምሮ የወረዳ አመራርና አድናቂዎቹ በጂንካ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በቦታው በመገኘት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።
ድሽታ ጊና ሙዝቃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአገር አልፎ ዓለም አቀፍ ዝናን በማትረፉ ሙዚቃውን በርካቶች በመላው ዓለም እየተቀባበሉት ይገኛል።
ታሪኩ ጋንኪስ የተለያዩ ዝግጅቶች እንዲያቀርብ በተደረገለት ግብዣ ምክንያት ከጂንካ ከአንድ ወር በላይ ወጥቶ ከቆየ በኋላ ሲመለስ ነው መላው የዞኑ ሕዝብና አመራሮች እንዲሁም የሥራው አድናቂዎች ወጥተው አቀባበል ያደረጉለት።
“የምድር ሥራ እንጂ ዘር አያፀድቅም በእሱ ፊት፣ አዳም ወንድሜ ሄዋን እህቴ” ከግጥሙ ስንኞች መካከል መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያነቃነቀ ሲሆን በስራውም በጎሳ፣ በዘር እንዲሁም በብሔርና በአካባቢ ከመታጠር በአንድ አዳም እና ሔዋን የሰው ዘር አንድ መሆኑን ያም አንድ ኢትዮጵያ የሚል መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ኹላችንም አንድ አባት እና አንድ እናት አለን፤ ኹላችንም የአዳም ዘር በመሆናችን በመላው አገር ያለ ሕዝብ ሁሉ ይህ መልዕክት ይድረሰው ብሏል የድሽታ ጊና ሙዚቃ ባለቤት ታሪኩ ጋንኪስ።
ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013


