የዴሞክራሲ ተቋማት ካቀረቡት የበጀት ጥያቄ ከግማሽ በታች መፈቀዱ ተገቢ አለመሆኑ ተገለጸ

0
751

የበጀት ጥያቄው ዳግመኛ እንደሚታይ ተጠቁሟል

ለ2014 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት ጥያቄ ያቀረቡ የዴሞክራሲ ተቋማት ለገንዘብ ሚኒስቴር ካቀረቡት የበጀት መጠን ከግማሽ በታች መፈቀዱ ተገቢ አለመሆኑ ተገለጸ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2014 ረቂቅ በጀት ላይ ማክሰኞ ግንቦት 17/2013 ተወያይቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴው በውይይቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፌደራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፌደራል እንባ ጠባቂ ተቋም የ2014 ረቂቅ በጀት ላይ ነው የተወያየው።

በውይይቱ የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለ2014 የጠየቀው በጀት 211.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በገንዘብ ሚኒስቴር የተፈቀደለት በጀት 103 ሚሊዮን ብር ነው። የፌዴራል የስነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ደግሞ 300 ሚሊዮን 815 ሺሕ ብር እንዲፈቀድለት ጠይቆ 109 ሚሊዮን 587 ሺሕ ብር እንደተፈቀደለት ተገልጿል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 192 ሚሊዮን 800 ሺሕ ብር ጠይቆ የተፈቀደለት 92 ሚሊዮን 551 ሺሕ ብር መደበኛ በጀት መሆኑ ተመላክቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2014 መደበኛ በጀት 442 ሚሊዮን 194 ሺሕ ብር ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ፣ 337 ሚሊዮን 863 ሺሕ ብር እንደተፈቀደለት ተመላክቷል። በተጨማሪም የምክር ቤቱ የካፒታል በጀትን 174 ሚሊዮን 500 ሺሕ ብር እንዲመደብለት ጥያቄ አቅርቦ የተፈቀደለት የገንዘብ ጣሪያ 59 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ነው ቋሚ ኮሚቴው የገለጸው።

በሌላ በኩል የፌደራል እንባ ጠባቂ ተቋም የ2014 የበጀት ዓመት እንዲፈቀድለት ለገንዘብ ሚኒስቴር የጠየቀው 85 ሚሊዮን ብር ሙሉ በሙሉ ተፈቅዶ የዓመቱ በጀት እንደሚሆን ነው የተገለፀው። የእንባ ጠባቂ ተቋም የተፈቀደለት የ2014 በጀት 16 በመቶ እድገት እንዳለው ተጠቁሟል። ተቋማቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ያቀረቡት ረቂቅ የበጀት ጥያቄ ሥራቸውን በተጠናከረ ሁኔታ ለመስራት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል። በመሆኑም ገንዘብ ሚኒስቴር ያቀረቡትን የበጀት ጥያቄ ከግማሽ በታች ቀንሶ ማቅረቡ የተቋማቱን የወደፊት ሥራ የሚጎዳ ነው ተብሏል።

የ2014 በጀት ዓመት ፍላጎታቸውን ለገንዘብ ሚኒስቴር አቅርበው ከሦስት እጥፍ ገደማ ተቀንሶ የተፈቀደለት የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ 300 ሚሊዮን ጠይቆ የተፈቀደለት 109 ሚሊዮን ነው። ኮሚሽኑ አሁን ከሚሰራው ሥራ አንፃር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተፈለገ የጠየቀው በጀት መጽደቅ እንዳለበት የኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የዴሞክራሲ ተቋማት የጀመሯቸውን ሥራዎች ያለ አቅም ውስንነት ተግዳሮት ማስቀጠል እንዲችሉ የጠየቁት በጀት የማይፈቀድላቸው ከሆነ፣ ተቋማቱ ከባድ ፈተና እንደሚገጥማቸውና ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችል አቅም ሊያጡ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

በተቋማቱ የ2014 በጀት ዓመት ጥያቄ ላይ የተወያየው ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጥያቄ ያቀረቡ የዴሞክራሲ ተቋማት በበጀት ዓመቱ ውስጣዊ አደረጃጀታቸውን በማሻሻል ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን እንዳቀዱ መገንዘቡን ገልጿል። በመሆኑም ቋሚ ኮሚቴው የዴሞክራሲ ተቋማትን በበጀት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አሳስቧል። ገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ የ2014 በጀት እንዲፀድቅላቸው ከጠየቁት የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና በበጀት አመቱ ለመስራት ባሰበው ልክ በጀት የጠየቀ የፌደራል እንባ ጠባቂ ተቋም መሆኑን ጠቁሟል። ሌሎቹ ተቋማት የተጋነነ የበጀት ጥያቄ ያቀረቡ በመሆኑ እንደገና ማየት እንዳለባቸው እና ተቋማቱ ከተመደበላቸው በጀት በላይ የሚጠይቁና የማይታለፉ ስራዎች ካሉ በቂ ሰነድና ማብራሪያ ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቁሟል። ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የዴሞክራሲ ተቋማት በአገሪቱ የሚከሰቱ ቀውሶችን ለማርገብ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ በበጀትም ሆነ በሰው ሀይል ማጠናከር እንደሚገባ ገልጾ፣ በጀቱ በቀጣይ እንደሚታይ ጠቁሟል።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here