የሥርዓተ ጾታ ትምህርት ለማን?

0
921

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

እኩልነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የሰው ልጅ በምንም አይነት ሰው ሰራሽ ሆነ የተፈጥሮ ልዩነት እርስ በርሱ እንዳይበላለጥ የሚያስችል ነው። በዘር፣ በኃይማኖትና በጾታ የሰው ልጆች መበላለጥ የለባቸውም እየተባለ ይነገራል። ከነዚህ ዘመን አመጣሽ ትምህርቶች መካከል የጾታ እኩልነትን የሚሰብኩ ትምህርቶች መሰጠት ከጀመሩ ምዕተ ዓመት አይሞላቸውም።

በታሪክ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ ሴቶች ከወንዶች እኩል አለመሆናቸው በጣም የተጋነነ ከመሆኑ የተነሳ ከአፍሪካ ይብስ እንደነበር ይነገራል። እንግሊዝ አገር ሴቶች በፖለቲካው ዓለም ተሳትፎ ማድረግ ከጀመሩ 70 ዓመት አይበልጥም። አሁንም ድረስ አውሮፓ ውስጥ ከሥራ ክፍያና ከመሳሰሉት የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታዎች አኳያ ልዩነት ቢኖርም፣ አሁን በተሻለ ለውጥ ታይቶባቸዋል። በአንጻሩ በአፍሪካ ሴት ልጅ የተሻለ ክብር የነበራት ቢሆንም፣ እንደ ምዕራባውያኑ ለውጥ ስላልመጣና ባለበት ስለቆየ አሁን የሚፈጸም ባህላዊም ሆነ ኃይማኖታዊ መሰረት ያለው መድሎ ፊት ለፊት ገዝፎ ይታያል።

በአገራችን ንግስተ ሳባ እንደነገሰች ከተመዘገበበት ከ3ሺሕ ዓመታት ወዲህ በዘራቸው ነግሰው ሥልጣን የተቆናጠጡ እቴጌ ጣይቱንና እቴጌ ዘውዲቱን የመሳሰሉ ዝነኛ ሴቶች ከመኖራቸው ባሻገር፣ አምፃና በውጊያ ድል ነስታ በርካታ ወንድ ወታደሮችን ወደ ጦርነት መርታ ውጤት ያስመዘገበችው ዮዲት ወይም አስቴርን የመሳሰሉ ጉደኛ ሴቶችን ያበቀለች አገር ናት። የቀደመው ታሪካችን እየደበዘዘ ሥልጣኔ ባመጣው የምዕራባውያን ተጽእኖ ስር ስንወድቅ እንደነሱ ወይም እንደ አረቡ አገራት ባህል እየሆንን ሴቶቻችን እኩል ለማየት ተቸግረን ቆይተናል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሴት ተፈጥሮ ከሚገድባት ልዩነት በስተቀር በሁሉም ረገድ ከወንድ እኩል ተወዳድራ ማሸነፍ ትችላለች የሚል ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል። ወንድና ሴት እኩል በአንድ ሩጫ ተወዳድረው ይሸናነፉ የሚል አስተሳሰብ ሳይሆን፣ እኩልነት ማለት ፍትሐዊነትን ያነገበ ነው። ተፈጥሮ የሚገድባት ታይቶ ከወንድ ጋር ተፈጥሯዊ ተጽዕኖ በሌለበት እኩል የመሆን እድል ሊሰጣት እንደሚገባ የሴት መብት ተከራካሪዎች ይሟገታሉ። ይህን ለማሳካት የሥርዓተ-ጾታ ትምህርት ከልጅነት ጀምሮ ይሰጣል። በየመስሪያ ቤቱም የራሱ ቢሮ ተከፍቶለት፣ ተቋማትም ተመስርተውለት፣ ትምህርቱ እየተሰጠ የማብቃቱም ሂደት እየተከናወነ ይገኛል።

ከሥርዓተ-ጾታ ትምህርት ጋር በተገናኘ የሚሰጠው ትምህርት በቀደሙት ዓመታት ለሴቶች ብቻ በቅድሚያ ይሰጥ ነበር። በትምህርቱ መብታቸውን ያወቁ ሴቶች ቤታቸው ገብተው በባህሉ መሰረት መብት መንፈጉን ሳያውቀው የለመደው ወንድ ጋር ሲያጋጫቸው ታይቷል። አንዳንዶች የአገር መሰረት የሆነው ቤተሰብና ትዳር እንዳይፈርስ ቅድሚያ መብት ነፋጊ የሆነው ወንዱ ከተማረ ሴቶቹ ባይማሩ እንኳን እኩልነቱን ለማምጣት ይቀላል ይላሉ። አለማችን የወንዱ ስለሆነች ወንድ ካልፈቀደ ሴቶች ብቻቸውን ቢጥሩም ውጤታማ አይሆኑም በማለት ይህን ሀሳብ የሚደግፉ ሰዎች የተለመደውን አሰራር ይተቻሉ።

በአንጻሩ ወንዱን ብቻ ማስተማሩ እያወቀ ላይለወጥ ይችላል። መብት እንዲከበር ጠያቂ ከሌለ የሚሰጥ አይደለም በማለት የሴቶችን ቅድሚያ መማር የሚሞግቱ አሉ። በዘርፉ ልምድ ያካበቱ ደግሞ ኹለቱንም እኩል ማስተማሩ የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ማለት ግን በአንድ አዳራሽ ቀላቅሎ ሳይሆን የየሆዳቸውን ዘርግፈው እንዲወያዩ በተለያየ መድረክ ማድረጉን ይመክራሉ። በአንድ ወቅት የአንድ ገጠር ሴቶች ውኃ ለመቅዳት ሩቅ እንዳይሄዱ ተብሎ ቅርብ የተቆፈረላቸውን የውሃ ጉድጓድ ከመጠቀም ያቆማሉ። ለምን? ሲባሉ ሩቅ መሄዱ ከወንዶች ቁጥጥር ርቀን የሆድ የሆዳችንን እንደልብ ለመወያየት ይረዳናል ማለታቸው መዘንጋት የለበትም።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here