የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጉባኤው የፌደራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፅድቋል።
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴው በተለያዩ ጊዜያት ከአስረጂዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመላክ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገበትና በቂ ግብዓትም የተገኘበት መሆኑን ገልጸው ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አቡ ብርኪ ተናግረዋል።
በውይይቱም የጥብቅና ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አገልግሎት ላይ ሰፊ የሕግ ክፍተት እንዳለ ብሎም የአሰራር፣ በአንዳንድ ጠበቆች ላይ የብቃትና የሥነ-ምግባር ችግሮች እየተስተዋሉ መምጣቱን በጭብጥነት መለየታቸውን አብራርተዋል።
አያይዘውም የጥብቅና ፍቃዱ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር መሆኑ አገልግሎቱ በሚጠበቅበት ደረጃ እንዳያድግና የሙያ ነጻነቱን በጠበቀ መልኩ አገልግሎቱ እንዳይሰጥ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የጥብቅና ሕጎቹ አገሪቱ ካለችበት አጠቃላይ ኢኮኖሚዊ፣ ማኅበራዊና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አንጻር ሊኖሯት የሚያስፈልጉ የጥብቅና ድርጅቶችን በተደራጀ ሁኔታ የሚመሩ አለመሆናቸውን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በረቂቅ አዋጁም አንዳንድ አንቀጾችን ሙሉ በሙሉ በሌሎች አንቀጾች ከመተካት ጀምሮ በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አሳውቀዋል።
ምክር ቤቱ በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ላይ በመመርኮዝ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ የፌደራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳዳር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1249/2013 ዓ.ም. አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን የምክር ቤቱ መረጃ ያሳያል።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013


