በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ፣ በጭነት ተሸከርካሪ ተደብቆ ሲጓዝ የነበረ 123 ቱርክ ሠራሽ ሽጉጥን ጨምሮ ተተኳሽ ጥይቶችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ የመምሪያ የሚዲያና ኮሙኒክሽን ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ውብነህ አስናቀ ለኢዜአ እንደገለጹት ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያው የተያዘው እኩለ ቀን በሳንጃ ከተማ የፍተሻ ኬላ ላይ ነው፡፡
ፖሊስና የጉምሩክ አባላት በጋራ ባደረጉት ጥብቅ ፍተሻ፣ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-77550 ኢት በሆነ ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 123 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥና 250 የክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ተተኳሽ ጥይት ተይዟል።
የጦር መሳሪያውን ከምዕራብ ጎንደር ዞን ምድረ ገነት ከተማ፣ ወደ ደብረማርቆስ ከተማ ለማስገባት ታቅዶ ሲጓጓዝ እንደነበር ኮማንድሩ አስረድተዋል፡፡
ፖሊስ አሽከርካሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013


