አንድ ሰው ከኮቪድ አገግሞ ከወጣ በኋላ እስከ ሦስት ወር ድረስ ቫይረሱ ተያያዥ በሽታዎች አስከትሎበት ኑሮውን ሊቀጥል ይችላል።ይህ ደግሞ ‹‹ፖስት ኮቪድ ሲንድረም›› የሚባል ሁነት ነው። በኮቪድ 19 የተያዘ ሰው ከዳነ በኋላ ፖስት ኮቪድ ሲንድረም ማለትም የተለያዩ ተያያዥ የጤና እክሎች እንደሚኖሩት በጥናት መረጋገጡን በዘውዲቱ ሆስፒታል፣ ICMC፣ ያናት ኮቪድ ሴንተር በመሥራት የቆዩና ኹሉ ኬር የሚባል የማኅበራዊ ድረ-ገጽ አስተባባሪ በመሆን የሚታወቁት መርሃዊ በርሄ (ዶ/ር) ተናግረዋል። እንደ መርሃዊ ገለጻ ከሆነ በኮቪድ 19 ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ አብዛኛው ከኮቪድ ያገገሙ ሰዎችን በመመልከት ምን ምን ምልክቶች በተደጋጋሚ እንደሚስተዋሉ ለማወቅ ተችሏል።
በዚህም አንድ የኮቪድ ታማሚ በሚያገግምበት ጊዜ ሦስት አይነት ደረጃዎች ያሉ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ድንገተኛ የኮቪድ 19 ቫይረስ ሲይዛቸው በመጀመሪያ አራት ሳምንታት ውስጥ የሚፈጠር ነው።ሁለተኛው ደግሞ፣ እየቀጠለ ያለ ኮቪድ 19 ይባላል።ማለትም ከተመረመሩ ከአራት ሳምንት እስከ 12 ሳምንት የሚቀጥል ሲሆን፣ ሶስተኛው የረጅም ጊዜ ኮቪድ 19 ነው።ይህ ደግሞ ከ12 ሳምንት በላይ የኮቪድ ምልክቶች የሚቀጥለባቸው ናቸው ተብሏል። ‹ናሽናል ኢንስትቲዩት ፎር ኸልዝ ሪሰርች› በሚባል ተቋም በጥቅምት 2020 እንግሊዝ ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፣ አብዛኛው ሰው ከተመረመረ ከአንድ ወር በኋላ ከ10-20 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የተለያዩ ምልክቶችን ያሳዩ መሆናቸው ተመላክቷል።በሌላ ጥናት ደግሞ ከተመረመሩት ውስጥ 87 በመቶ ከ60 ቀን በኋላ በሽታው ጋር የተያያዙ ምልክቶች ታይቶባቸዋል።
እነዚህ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ከምልክቶቹ በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቀሰው ስንፈተ ወሲብ ሲሆን፣ ‹ኢንዶቴሊያል ዳሜጅ› ወይንም ብልት አካባቢ ላይ የሚገኙትን የደም ስሮች በሽታው ስለሚያጠቃ ወንዶች ላይ ብቻ የሚከሰት ነው። በመቀጠል የድካም ስሜት ነው።ታክመው ነጻ (ኔጌቲቭ) ከተባሉ በኋላ የሚሰማቸው ነው።ሶስተኛው ከልብና ከሳንባ ጋር በተገናኘ ትንፋሽ ማጠር፣ ያለማቋረጥ ማሳል እና የደረት ህመም ናቸው ተብሏል። በተጨማሪም ራስ ምታት ያስከስታል።እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ላይ መርሳት ችግር፣ የአይን ብዥታ ፣ አላግባብ የሆነ መንቀጥቀጥ እንዲሁም በአግባቡ መቅመስ እና ማሽተት አለመቻል ይጠቀሳሉ። ለእንደዚህ አይነት በሽታ ተጋላጭ የሚሆኑት ደግሞ 70 በመቶዎቹ ጽኑ ህሙማን የነበሩ ሲሆኑ፣ ከወጡ ከ4 እስከ 8 ሳምንታት በኋላ የሚከሰት ነው።በተጨማሪም የልብና የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ምልክቶቹ ይከሰትባቸዋል። እነዚህ የተጠቀሱት በሽታዎች የኮቪድ መያዝን ተከትሎ መምጣታቸውን ለማወቅ ግለሰቡ ቅድሚያ በነዚህ በሽታ ቀድሞ አለመያዙን ማረጋገጥ ይኖርብናል ሲሉ መርሃዊ ያነሳሉ።
መፍትሄው ምንድን ነው?
በመጀመሪያ የበሽታ መከላከል አቅማችንን ማዳበር ነው።ለዚህ ደግሞ ቫይታሚን ሲ፣ ዚንክ፣ እና ቫይታሚን ዲ መውሰድ ይገባል።እነዚህ የሚገኙት ደግሞ ከምግብ ነው።እንደ ብርቱካንና ሎሚ ያሉ ፍራፍሬዎችን መመገብና የፀሃይ ሙቀት ማግኘት ይገባናል ሲሉ መርሃዊ ይናገራሉ።
አገግመን ከወጣን በኋላም ቢሆን የበሽታ የመከላከል አቅማችንን መጨመር አለብን።በመቀጠል ደግሞ የደረት እንቅስቃሴዎችን መሥራት ነው።የአዕምሮ ስፔሻሊስቶችን ማናገር፤ በሽታው ጭንቀት እና መረበሽ ስለሚፈጥር ምክር በማግኘት እንዲሻላቸው ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ መርሃዊ ጠቁመዋል።
በኮቪድ 19 የተጠቃ ሰው ከበሽታው ለማገገም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ ነው።ከሚያደርጋቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካከል አንድ እጅን ደረት ላይ በማድረግ አንድ እጅን ደግሞ ሆዳችን ላይ በማድረግ አየር ማስወጣትና ማስገባት ጠቃሚ ነው።
ሌላው ደግሞ አየር በአፍኝጫችን ቀስ እያልን በማስገባትና በማስወጣት ልምምድ ማድረግ ነው።ይህ የአተነፋፈስ ሥርዓት ቶሎ እንዲመለስ ይረዳናል ሲሉ ገልጸዋል። በቤት ውስጥ ራስ ምታትን የምናስታግስበት መንገዶች መካከል በንጹህ ጨርቅ ውኃ በማድረግ፣ በቂ ፈሳሽ በመጠጣት፣ ለብ ባለ ውኃ ገላችንን በመታጠብ፣ በቂ እንቅልፍ በመተኛት እና የጤና ባለሙያዎችን በማማከር ማስታገሻዎችን መውሰድ ይመከራል።
በተጨማሪም የአመጋገብ ሥርዓታችን ላይ በሽታ ተከላካይ ምግቦችን ማካተት አለብን።እንደ ሎሚ እና ብርቱካን አይነት ፍራፍሬዎች ቫይታሚን ሲ ስላላቸው ነጭ የደም ሴሎችን ማነቃቃት ይችላሉ።ፓፓዬ በውስጡ ፓምፔን የሚባል ንጥረ ነገር ያለው ሲሆን፣ በኮቪድ ጊዜ የሚመጣ የጨጓራ መቃጠልን ያስቀራል።በተጨማሪም ፓፓያ ፖታሽ፣ ቫይታሚን ቢ እና ፎሊክ በውስጡ ስላለው በሽታ የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው። ነጭ ሽንኩርት ደግሞ ደብሊው ቢሲ የተባለውን የበሽታ የመከላከል አቅማችንን በማነቃቃት ከፍተኛ ከሆነ ሳል በቶሎ እንድናገግም ያደርጋል።
ሌላው ቲማቲም 16 ሚ.ግ. ቫይታሚን ሲ ስላለው የነጭ የደም ህዋሶችን በሽታ የመከላከል አቅም ይጨምራል ሲሉ መርሃዊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የህክምና ባለሙያዎች ከኮቪድ–19 እያገገሙ ባሉና ባገገሙ ህመምተኞች ላይ ብላክ ፈንገስ የተባለ በሽታ እያዩ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።በህክምና ቋንቋ ሙክሮሚክስ የሚሰኘው ይህ በሽታ ሰው ለይቶ የሚያጠቃ ሲሆን ስኳር፣ ኤች. አይ.ቪ. እና ካንሰር ያለባቸውን ሰዎች በይበልጥ ያጠቃል። ይህ ደግሞ በኮቪድ -19 በጽኑ ህመም ላይ የቆዩ ሰዎች የሚወስዱትን ኃይል ሰጪ መድኃኒት ተከትሎ የሚመጣ መሆኑን ጥናቶች አሳይተዋል። የኮቪድ-19 ምልክቶች ትኩሳት፣ ሳል፣ የምግብ መፈጨት ችግር፣ ማስመለስ ተቅማጥ፣የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የነርቭ ምልክት፣ ራስ ምታት እና የዕይታ ችግር መሆናቸው ይታወቃል።
![]() | ![]() |
ባለፉት ኹለት ዓመታት ውስጥ ከኹለት ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት መገንባታቸው ተገለጸ
ከ2009 ጀምሮ እስካሁን 2864 የጤና ተቋማት የተገነቡ ሲሆን፣ 76 በመቶዎቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆኑ፣ የቀሪዎቹም አፈጻጸማቸው ከ90 በመቶ በላይ ነው ተባለ። የጤና ተቋማቱ ግንባታም በጤና ሚኒስቴር እና በክልሎች በጋራ ወጪ የሚሸፈን መሆኑን በመግለጽ ፣ ያልተጠናቀቁ ግንባታዎችም በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል። ላልተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት ከሆኑት ውስጥ፣ የአንዳንድ የሥራ ተቋራጮች ድክመት፣ በአንዳንድ አከባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮች፣ ፋብሪካዎች የገጠማቸው አስፈላጊ ግብአቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ዋናዋናዎቹ ናቸው።
የጤና መሠረተ ልማት የ2013 ዓ.ም የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ግምገማ ተካሂዷል። በጤና መሠረተ ልማት የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር የተገኙበት ሲሆን፣ ሕብረተሰቡን ማዕከል ያደረጉ ነባርና አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች ማስፋፊያ፣ የጤና ባለሙያዎች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ለጤና ጣቢያዎች የንፁህ ውሀና የመብራት አቅርቦት ሥራ፣ እንዲሁም የተጎዱ ጤና ጣቢያ እድሳቶች አስመልክቶ የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም፣ የፋይናንስ አጠቃቀም፣ የነበሩ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች በዝርዝር ሪፖርት በማቅረብ ውይይት ተደርጎበታል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አለምፀሐይ ጳውሎስ ባደረጉት ንግግር፣ የጤና ሴክተሩ ባለፉት ዓመታት ከሠራቸው በርካታ ሥራዎች ውስጥም፣ ጤና ተቋማትን ተደራሽ ማድረግ እና የጤና አገልግሎት ሽፋንን ለማሣደግ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የመጡ ውጤቶች አበረታች መሆናቸዉን ጠቅሰዋል። የጤና መሠረተ ልማት በፍትሐዊነትና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የክልሎችን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያደረገ፣ ለቀጣይ አስር ዓመታት የሚያገለግለን የጤና መሠረተ ልማት ፍኖተ ካርታ አስፈላጊ በመሆኑ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልፀዋል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና መሰረተ ልማት ዳይሬክተር ኢንጂነር ታደሠ የማነ እንደተናገሩት የአገራችን የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ፣ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት፣ የጤና መሠረተ ልማት ማስፋፋትና ሕብረተሰቡ አገልግሎቱን በቅርበት እንዲያገኝ ማድረግ አንዱ በመሆኑ የጤና ሚኒስቴር በኹሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳደሮች የጤና መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ጥገናና ማስፉፊያ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013





