ባለፉት ኹለት ዓመታት ውስጥ ከኹለት ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት መገንባታቸው ተገለጸ
ከ2009 ጀምሮ እስካሁን 2864 የጤና ተቋማት የተገነቡ ሲሆን፣ 76 በመቶዎቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆኑ፣ የቀሪዎቹም አፈጻጸማቸው ከ90 በመቶ በላይ ነው ተባለ። የጤና ተቋማቱ ግንባታም በጤና ሚኒስቴር እና በክልሎች በጋራ ወጪ የሚሸፈን መሆኑን በመግለጽ ፣ ያልተጠናቀቁ ግንባታዎችም በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል። ላልተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት ከሆኑት ውስጥ፣ የአንዳንድ የሥራ ተቋራጮች ድክመት፣ በአንዳንድ አከባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮች፣ ፋብሪካዎች የገጠማቸው አስፈላጊ ግብአቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ዋናዋናዎቹ ናቸው።
የጤና መሠረተ ልማት የ2013 ዓ.ም የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ግምገማ ተካሂዷል። በጤና መሠረተ ልማት የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር የተገኙበት ሲሆን፣ ሕብረተሰቡን ማዕከል ያደረጉ ነባርና አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች ማስፋፊያ፣ የጤና ባለሙያዎች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ለጤና ጣቢያዎች የንፁህ ውሀና የመብራት አቅርቦት ሥራ፣ እንዲሁም የተጎዱ ጤና ጣቢያ እድሳቶች አስመልክቶ የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም፣ የፋይናንስ አጠቃቀም፣ የነበሩ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች በዝርዝር ሪፖርት በማቅረብ ውይይት ተደርጎበታል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አለምፀሐይ ጳውሎስ ባደረጉት ንግግር፣ የጤና ሴክተሩ ባለፉት ዓመታት ከሠራቸው በርካታ ሥራዎች ውስጥም፣ ጤና ተቋማትን ተደራሽ ማድረግ እና የጤና አገልግሎት ሽፋንን ለማሣደግ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የመጡ ውጤቶች አበረታች መሆናቸዉን ጠቅሰዋል። የጤና መሠረተ ልማት በፍትሐዊነትና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የክልሎችን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያደረገ፣ ለቀጣይ አስር ዓመታት የሚያገለግለን የጤና መሠረተ ልማት ፍኖተ ካርታ አስፈላጊ በመሆኑ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልፀዋል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና መሰረተ ልማት ዳይሬክተር ኢንጂነር ታደሠ የማነ እንደተናገሩት የአገራችን የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ፣ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት፣ የጤና መሠረተ ልማት ማስፋፋትና ሕብረተሰቡ አገልግሎቱን በቅርበት እንዲያገኝ ማድረግ አንዱ በመሆኑ የጤና ሚኒስቴር በኹሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳደሮች የጤና መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ጥገናና ማስፉፊያ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


