“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
በአስርት አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲ ጉባኤዎችን፣ ክርክሮችን፣ ቅስቀሳዎችን ለተከታተለ ሰው አንድ ጎልቶ የሚንጸባረቅ ጉዳይ አለ። በፖለቲካው ዓለም የአንበሳ ድርሻውን የሚይዙት ወንዶች ከመሆናቸው በተጨማሪ በማዕከላዊ እና በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነታቸው የሴቶች ቁጥር የተመናመነ እና/ወይም በአንዳንድ ፓርቲዎች እንደሚታየው የሉም ማለት ይቻላል። አገሪቱ ምርጫ በምታካሂድበት ወቅት የሚስተዋለው የሴቶች ተሳትፎ ክፍተት በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ ይወጣል፡፡ ፓርቲዎቹ የሚያቀርቧቸው ሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎች አናሳ መሆኑንም ማስተዋል ይቻላል።
በንጉሱ አገዛዝ ዘመን የነበረውን የሴቶች የፓርላማ ተሳትፎ ቁጥር በምንመለከትበት ወቅት ከ240 የፓርላማ አባላት መካከል 2ቱ ሴቶች የነበሩ ሲሆን፣ በደርግ ጊዜ ደግሞ ከ835 የሸንጎ አባላት መካከል 14 ሴቶች ይገኙበታል። ከ26 አመታት በፊት የነበረውን የ1987 ዓ.ም ምርጫን እንመልከት። በዚህ አመት በተደረገው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ 536 ወንዶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን፣ የሴቶች ቁጥር ደግሞ 10 ነበር። በ2007 ወይም በአሁኑ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሴቶች ያላቸው ቁጥር 212 ወይም በመቶኛ ሲሰላ 38.8 በመቶ ነው።
በተለይም የሥርዓተ ፆታ የኃይል ሚዛን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት መዋቅራዊ የሆኑ የፖሊሲ ለውጦች ያስፈልጋሉ በሚባልበት ወቅት ሴቶች የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው መወሰን አልቻሉም ይባላል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገር አቀፍ ብሔራዊ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናት፤ ምርጫው የተቆረጠበት ቀን ሊደርስም ኹለት ቀናት ያህል ቀርቶታል። ከፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ በተጨማሪ የወንዶችንና የሴቶችን ግንኙነት ወይም ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለውን ቦታ አስመልክቶ በሚወስነው አባዊ
ሥርዓት (ፓትሪያርኪ) ምክንያት ሴቶች በፖለቲካው፣ በትምህርት እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ተሳታፊነታቸው ወደ ኋላ የቀረ እንዲሆን ተድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ በሰፈነው ኢ-ፍትሃዊ የሥርዓተ-ፆታ የኃይል ሚዛን ለተለያዩ መድልዎችና ፆታዊ ጥቃቶችም ሰርዓቱ እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል። የሥርዓተ-ፆታ ሚዛን ኃይል አለመመጣጠን በተለይም የሚገለጽበት አንዱ ሁኔታ በሴቶች ላይ ያለው ተደራራቢ የሥራ ጫና ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ ለሴቶች እፎይታ አግኝተው በሌሎች መድረኮች እንዳይሳተፉ አድርጓቸዋል።
ሁኔታዎች የተቀየሩት የሴቶች መብትን እንደ ሰው መብት ወይም ደግሞ እንደ ፖለቲካዊ ጥያቄ ባዩ አንዳንድ የፖለቲካ ንቃተ ህሊናቸው ከፍ ባሉ አመራሮች ምክንያት እንደሆነም የታሪክ ተንታኞች ያስረዳሉ። ከአስርት አመታት በኋላ ይኸው ሴቶችን ከቤት ሥራዎች ድርሻ ጋር የማያያዙ ባህልም ሆነ ልምድ አልቀረም ። ሰኞ ሰኔ 14/2013 ከሚደረገው ምርጫ በኋላ በሴቶች የሚያዝ የምክርቤት ወንበር መስፋት እንዳለበት ይታመናል፡፡


