“ማን ተመረጠ ማን ለእኛ ትርጉም አይኖረውም”

0
1297

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስ መምህርነት ለረዥም አመታት አገልግለዋል። ከሙያቸው ባሻገር በፖለቲካው አለም ለበርካታ አመታት የቆዩ ሲሆን፣ በዘንድሮው ምርጫ የማይወዳደሩት የኦፌኮና የመድረክ ሊቀመንበር ናቸው። የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ የማይቻልበት ጊዜ ላይ እንደመሆናችን ከእሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል።

የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት እንዴት ይገመግሙታል?
ምርጫውን በዚህ ደረጃ እንደሚገፉበት ባላውቅም ምርጫው የአገሪቱን መሠረታዊ ችግሮች የሚፈታ አይመስለኝም። የበለጠም ሊያባብስ ይችላል። በአጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩ ከጠበቅነው በላይ በፍጥነት እየጠበበ ስለሄደ፣ ቢሮዎቻችንም በስፋት እየተዘጉ ስለሄዱ፣ አባላቶቻችንም ስለታሰሩ፣ ምርጫ ቦርድም ምርጫ አስፈጻሚዎች ብሎ ያሰማራቸው ከየት እንደመጡ የማይታወቁና አንዳንዶቹን ደግሞ ሥራ አጥ ብሎ ምርጫ ቦርድ ሰብስቦ ስላሰማራና በሌሎች ብዙ ችግሮች ምክንያት ሂደቱ ስለተተበተበ ምርጫው ፍትሐዊና ነጻ የመሆን እድሉ እየመነመነ መጥቷል። በዚህ ሳቢያ ተሳትፏችን ጥቅም ይሰጣል ብለን ማመን ስላልቻልን ሶስት መሰረታዊ ምክንያቶችን አስቀምጠን ራሳችንን ከምርጫው አግልለናል። አንደኛው ዘላቂ መረጋጋትና ሰላም እንደማያመጣ በማሰባችን ሲሆን፣ ሁለተኛው በ3ሺሕ ዘመን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ ትወለዳለች የተባለው ለእኛ እጅግ በጣም አጠራጣሪ በመሆኑ፣ ሶስተኛ ትርጉም ወዳለው ልማትና ብልጽግና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለይም ወጣቶች መዞር ይችላሉ የሚለው አጠራጣሪ ስለሆነ ነው። በአጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳር የሚባለው በዚህ ምርጫ ስለተዘጋ ነው ከምርጫው የወጣነው። በእኛ ግምት በተለያየ ጊዜ እንደተናገርነው ምርጫው በብሔራዊ መግባባት ካልታጀበ ትርጉም ያለው ምርጫ ሊሆን እንደማይችል አምነን ተቀባይነት እንዲያጣ ተገደን ከመውጣት ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረንም።

ፓርቲያችሁ ራሱን ካገለለ ወዲህ ያለውን ሂደት እንዴት አያችሁት?
በምርጫው የእኛ መኖር አለመኖር ሳይሆን 50 በመቶ በሚሆን አካባቢ ምርጫ አይኖርም። ለምሳሌ፣ ትልቁ የአገሪቱ ክፍል የሚባለው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ አንድ ፓርቲ ነው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው። ትግራይ በሙሉ ከጨዋታው ውጭ ነው። ቤኒሻንጉል በጦርነት የተጠመደ ነው። ቅማንትንና የኦሮሚያ ልዩ ዞንን የመሳሰሉ አንዳንድ የአማራ አካባቢዎችም ከምርጫው ውጭ የሆኑ ይመስሉኛል። ሱማሌ ክልልም ለሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል። ተወዳዳሪ ዕጩዎች የተመዘገቡትም ከክልሉ ውጭ ነው። በአጠቃላይ ከ50 በመቶ በላይ በሚሆኑ አካባቢዎች ምርጫው የሚካሄድ አይመስልም። ይህ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያሳይ ነው። አንዳንዶች ምርጫው የተበላ እቁብ ነው እንደሚሉት ነው። በዛም ሆነ በዚህ ምርጫው ሰላማዊ የሆነች ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመውለድ፣ ሕዝብ የተሻለ ፖለቲካ አግኝቶ በሙሉ ስሜቱና ልቡ ወደ ልማትና ብልጽግና እንዲያመራ የሚያደርግ ሁኔታን አይፈጥርም። በአጠቃላይ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ እንዲባል አስቻይ ሁኔታ የለም።

በቀጣይ ምን ለማድረግ አስባችኋል?
እኛ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግላችንን መቀጠላችን አይቀርም። እስከዛሬ ስንታገልበት በነበረው መንገድ ሕዝቡ ለመብቱ፣ ለነጻነቱና ለክብሩ እንዲታገል መሥራቱን እንቀጥላለን።

ከውጭ ጉዳይ ጋር በተገናኘ የዲፕሎማሲ ግንኙነታችን እየሻከረ መጥቷል። በዚህ ጉዳይ ያላችሁ አስተያየት ምንድን ነው?
ይህ የሆነው በኹለት መንገድ ነው። አንደኛው፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ድሮውንም ቢሆን በችግር የተተበተበ ስለሆነ ነው። ለገዢው ፓርቲ ታማኝ የሆኑ ካድሬዎች ታማኝነታቸው እንጂ የእውቀትና የችሎታ ጥያቄ ስለማይኖርባቸው የፈጠረው ችግር ነው። ሌላው መሬት ላይ ያለው እውነታ ኢትዮጵያ ያለችበት ኹኔታ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር የሚጋብዝ አይደለም። የምዕራቡ ዓለም ሁኔታ “አትተራረዱ፣ አትጠፋፉ፣ ሰላም ፍጠሩ” የሚል አይነት ግፊት ይመስላል። በዚህ በኩል ደግሞ “ኢትዮጵያ ልትወረር ነው፤ ጣልቃ ገብነት ነው፤ ሉዓላዊነታችን ተደፈረ፡፡” ሲሉ እሰማለሁ። ምንድን ነው ችግሩ ተብሎ ቁጭ ተብሎ ያልታሰበበትና መፍትሄ ሊያመጡ የሚችሉ ሰዎች እያነሱ መሄዳቸውን ነው የሚያሳየው። ይህ መሆኑ ለአገሪቱ እጅግ በጣም ይጎዳል። በተለይ ከአሜሪካኖች ጋር የተገባው ቀልድ መልክ ካልያዘ ውድ ዋጋ የሚያስከፍለን ይመስለኛል።

በትግራይ እየሆነ ያለውን እንዴት ያዩታል?
በትግራይ ጉዳይ ሐሳባችንን ከመጀመሪያውም አሳውቀናል። ወደ ጦርነት ከመገባቱ በፊት ለብሔራዊ መግባባቱ ቅድሚያ እንዲሰጥና ሁኔታዎችን እንዲያመቻች መንግሥትን መክረን ነበር። ጦርነቱም እንደፈነዳ በጦርነት ከመግፋት ወደ ተኩስ ማቆምና ያለውን ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልጋል ብለን መግለጫዎችን እስከማውጣት ደርሰን ነበር። ይህን በማድረጋችን ካድሬዎቹ ተናደውብን በጣም ተንጫጭተው ነበር። የህወሓት ደጋፊ ነው ብለው ወደ መደምደምም ሄዱ። በእኛ እይታ ችግሩ ፖለቲካዊ ነው። በኢሕአዴጎች መካከል የተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ያመጣው ጣጣ ነው። ፖለቲካዊ ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ መፍታቱ ይጠቅማል ብለን ስንመክር የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ባይደረግም አቋማችን ይህ ነው።

በምርጫው ከሚወዳደሩት መካከል ደጋፊዎቻችሁን እገሌ ይሻላል ምረጡት ያላችሁ ነበር?
እኛ ምርጫውን ራሱን ስላላመንበት ማን ተመረጠ ማን ለእኛ ትርጉም አይኖረውም። ያሉብንን መሰረታዊ ችግሮች ስለማይፈታ ለውጥ አያመጣም። ገዢው ፓርቲ እንደሚመረጥ እናውቃለን። ይህ ሁሉ ጣጣና ፍጭት ገዢው ፓርቲ እንዲመረጥ ለማድረግ የተሄደበት መንገድ ነው እንዲህ አይነት ጣጣ ውስጥ የከተተን። ያን ያህል መፍትሄና ለውጥ ላያመጡ ምርጫው ውስጥ የገቡትን እግዚአብሔር ይርዳቸው ከማለት ውጭ ብዙ ማለቱ አይጠቅመንም።

ደጋፊና ተከታዮቻችሁ በምርጫው እንዲሳተፉ ነው ወይስ እንደናንተ ራሳቸውን እንዲያገሉ ነው የምትፈልጉት?
እኛ ለራሳችን ምርጫው ትርጉም ያለው ስለማይሆን፣ የአገሪቱንም መሰረታዊ ችግሮች ይፈታል ብለን ስላላመንን ተገፍተን ወጥተናል። ተከታዮቻችንና አባሎቻችን ይህንን አይተው የራሳቸውን ውሳኔ መወሰን የሚችሉ ይመስለኛል።
በአጠቃላይ ይህ ምርጫ ተብሎ ቅርጫ እንኳን በማይመስል ኹኔታ እየገፉበት ለበለጠ ቀውስ፣ ለበለጠ የፖለቲካ አጣብቂኝና አደጋ እያዘጋጁት ነው። ባለፉት አመታት ችግሮቻችንን መፍታት አቅቶን ከቀውስ ወደ ቀውስ እየተሸጋገርን ኖረናል። አሁን በሰከነ አእምሮ ቁጭ ተብሎ አስቦ ችግሮቹን ለመፍታት መጣሩ ይመረጣል። ምርጫው ውስጥ የገቡትም ሆኑ ያልገቡ ኃይሎች አሁንም ቢሆን ወደ ብሔራዊ መግባባት ገብተው ሌላ ምርጫ ለማካሄድ መዘጋጀቱ ሕዝቡንም ይጠቅማል የሚል ምክር አለን።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here