“ምርጫ የሚያሸንፍ ሕገ-መንግስቱን ሊያሻሽለው አይችልም”

0
1124

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዋቂነትን እያተረፉ ከመጡ ወጣት ጋዜጠኞች መካከል መዓዛ መሐመድ በግንባር ቀደምነት ትሰለፋለች። የዜጎች መጨፍጨፍ ከሚያንገበግባቸው ጥቂት ጋዜጠኞች አንዷ የሆነችው ይህች ጋዜጠኛ፣ የበርካቶችን ድምጽ ለሕዝብ ለማድረስ ከመቻሏ ባሻገር በተለያዩ መድረኮች እየተገኘች አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግ ትታወቃለች። ምርጫውን በተመለከተ ያላትን አስተያየት እንድትሰጠን የአዲስ ማለዳ እንግዳ አድርገናታል።

አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን እንዴት ትገመግሚዋለሽ?
ስለ አጠቃላይ ምርጫ ሂደቱ አሁን ቀናት በቀሩበት ሁኔታ ብዙ ማለት ባይቻልም፣ ከለውጡ ወዲህ ምርጫውን በብዙ ተስፋና በብዙ ስጋት ታጅበን የጠበቅነው ነበር። ከ52 በላይ ፓርቲዎች እንደሚወዳደሩ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ተከትሎ ሂደቱ ሲጠበቅ የነበረ ነው። እንደእኔ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ምርጫ ቦርድ ኹለት ሥራዎችን ሲሠራ ነበር። አሠራሩን እያሻሻለ እግረ መንገዱንም ምርጫ እያካሄደ ነበር። በዚህ ሂደት ራሱ ምርጫ ቦርድ ሊቋቋማቸው ያልቻሉ ችግሮች ተከስተዋል።

የጥራት ብቻ ሳይሆን ቴክኒካል ችግሮች ስለነበሩ አሁን ለምንሰማቸው እክሎች ዳርጓል። ዛሬ እያጋጠሙ ካሉት ችግሮች መካከል ከኅትመት ወረቀት ጉድለት ጀምሮ በየቦታው ማለት በሚቻል መልኩ በበርካታ ቦታዎች ምርጫውን ማካሄድ አለመቻሉ፣ ከቁጥጥሩ ውጭ የሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው መገኘታቸው፣ በነዚህን በመሳሰሉ እክሎች ምርጫው በከፊል ለሌላ ቀን እንዲተላለፍ መደረጉ ከመጀመሪያው ምርጫ ቦርድ አቅሙን ማጎልበት አለመቻሉን የሚያሳይ ነው። ኹለቱንም ሥራዎች አንድላይ ለማስኬድ መሞከሩ በራሱ ችግር ነበር።
ሌላኛው መሠረታዊ ችግር፣ የአገሪቱን ችግር በምርጫ መፍታት በማይቻልበት ሁኔታ ምርጫውን ማካሄድ ወይም አለማካሄድ የሚሉ የኹለት ወገን ክርክሮች መፍትሄ ሳያገኙ መቀጠላቸው ነው። ምርጫ ቦርድ የእለት ተለት ቢሮክራሲ ሥራዎቹ ላይ አተኮረ እንጂ እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን ከግምት በመውሰድ ነባራዊውን የጸጥታ ሁኔታ ያመሳከረና የተረዳ ተግባር እየፈፀመ አይደለም። ብዙ ችግሮችን ይዞ የመጣ ምርጫ መሆኑ ቢታወቅም፣ ምርጫ ቦርድ ሥራውን በተለያዩ አካባቢዎች በአግባቡ ማከናወን እንደማይችል ታውቋል። ትግራይ ክልል፣ ሱማሌ ክልል፣ አማራ ክልል ከ8 ወረዳዎች በላይ ምርጫ አይካሄድባቸውም መባሉ አዲስ ነገር እንዳንጠብቅ ያደርገናል። ምርጫ በሚደረግባቸውም አካባቢዎች አሁንም የጸጥታ ችግር መኖሩም ይታወቃል። በኦሮሚያ ክልል የተወዳዳሪዎችን አቅም ማጣት አይተናል። በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰባስበው በሰጡት መግለጫ ስለምርጫው ያላቸውን አቋም አይተናል። ዝቅተኛ መስፈርትን አያሟላም ማለታቸው ጥያቄ ቢፈጥርም፣ ችግሩን እያወቁ የሚገቡበት ምርጫ ነው። ብዙ ችግሮች ጥላቸውን ባጠሉበት በዚህ ጊዜ ይካሄዳል መባሉ ለኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያለ ነገር ነው።

ምርጫ ቦርድ የማያውቃቸው ጣቢያዎች መቋቋማቸው ምንን ያመለክታል?
ምርጫ ቦርድ ሥራውን እየሠራ ያለው እንደማንኛውም ድርጅት ቢሮክራሲው ላይ አተኩሮ በመሆኑ፣ አንድ በሽግግር ላይ ያለችን ትልቅ አገር ምርጫ የሚመራ አይመስልም። ከመጀመሪያው ጀምሮ በርካታ አይኖች እንዳረፉበት አልተረዳም። ከመጀመሪያው ጀምሮ ራሱን እንዳዲስ ማቋቋም ያልቻለ ተቋም ይህን ትልቅ ኃላፊነት መወጣት ይችላል ወይ ብለን ስንጠይቅ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ አለመቻሉ እንደተገመተው ታይቷል።

ምርጫ ቦርድ በየቦታው ያሉ ግጭቶችን ማስቆም እንደማይጠበቅበት ግልጽ ነው። ይህ የመንግሥት ሥራ ነው። ይህ ቢሆንም ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫውን ማካሄድ እችላለሁ ወይ ብሎ ቅድሚያ ማጥናት ነበረበት። ምርጫ ቦርድ ማለት ወይዘሮ ብርቱካን ብቻ አይደሉም። እስከታች ቀበሌ ድረስ ሥራውን እንዴት ማከናወን እንደሚችል መገምገም ነበረበት። ለታይታና ለሪፖርት ከሚሆን ሥራ ውጭ እውነቱን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። እነሱ ሳይዋሹ ባወጡት መረጃ መሠረት የሚወጡ መረጃዎች የሚገርሙ ናቸው። በሌሎች አቅሙ ባላቸው ቢጠና ደግሞ የባሰ ነገር ሊኖርም ይችላል። ይህ አይነቱ ነገር ቦርዱ ላይ ያለውን አመኔታ ይቀንሳል። በአጠቃላይ የማስፈምጸም አቅም አለው ወይ ብለን ካየነው እንድናዝን የሚያደርግ ነገር ነው የተፈጠረው።

ምርጫው በኹለት ዙር መካሄዱስ እንዴት ይታያል?
እኔ በምርጫው ላይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ስላልተማመንኩ አሁን የተቀየረ ነገር የለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርጫ ቦርድ በየቀኑ የተለያዩ መግለጫዎችን እየሰጠ ነው። የምርጫ ውጤትን በተመለከተ ጳጉሜ 1 ድረስ መጠበቅ እንደሚኖርብን አሳውቋል። ይህ መሆኑ የነበረን ጥርጣሬ እንዲጨምር አድርጓል። ታማኝነቱን የሚያሳጣ ከመሆኑ ባሻገር ለድህረ ምርጫ ግጭት የሚዳርግ ይመስለኛል።

አሁን ካለን የውጭ ግንኙነት አኳያ ምርጫው በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚኖረው ተቀባይነት እንዴት ይሆናል ትያለሽ?
አሁን አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ ያለችበት ጊዜ እንደመሆኑ ስለምርጫችን ጆሮ የሰጠ የውጭ አካል አለ ወይ? ነው ዋናው መሰረታዊ ጥያቄ። “እነሱ ተቀባይነቱን አሳወቁን አላሳወቁን ለእኛ ተራ ጉዳይ አይደለም” ማለቱ ተራ መመጻደቅ ነው። ያላቸውን ተጽእኖ በግልጽ የምናውቀው ስለሆነ መመጻደቁ ተገቢ አይደለም። ምዕራባውያኑ ስለምርጫችን ሳይሆን የሚያወሩት መጀመሪያ ችግራችሁን ፍቱ እያሉ ነው። ምርጫውን በተመለከተ ይህን እናንተ አድርጉ እኛ ይህን እናደርጋለን ሲሉ አልተሰሙም። ምርጫውን ትተው እነሱ የሚያወሩት ስለሌላ ስለሆነ ተቀባይነት ይኖረዋል ለማለት ይከብዳል። እነሱ የሚጠይቁት በምርጫው የሚፈታ ከሆነ እውቅና ሊሰጡት ይችላሉ። እውነታው ግን ችግሩ በምርጫ የሚፈታ አለመሆኑ ነው። እንደውም ምርጫው ሊያባብሰው የሚችለው ችግር ውስጥ ነን። ለምሳሌ ሕገ-መንግስቱን ከማሻሻል አኳያ፣ ምርጫ የሚያሸንፍ ሕገመንግስቱን ሊያሻሽለው አይችልም። ምክንያቱም እንዲሻሻል የሁሉም ክልሎች ይሁንታ ስለሚያስፈልግ ነው። ትግራይ ክልል በኹለቱም ዙር ምርጫ ስለማይደረግ ያለክልሉ ድምፅ ሊሻሻል አይችልም። ይሀን የመሳሰለ ችግርን የማይፈታ ምርጫ ስለሆነ የምናካሂደው ያረፈብንን ዓለም አቀፍ ጫናም አይፈታም።

ሽንፈትን የመቀበል ባህላችንን እንዴት ታይዋለሽ?
ሽንፈትን የመቀበል ባህል በፍጹም የለንም። የምርጫው ትልቁ ስጋቴ ይህ ነው። ምርጫውን በሙሉ አሸናፊነት እንደሚወጡት የሚያመላክቱ ንግግሮችን ስሰማ ስጋቴ እያደር ይጨምራል። ትላንት የአንድ የበላይነት ስንለው የነበረውን አይነት የሚደግም ተግባር በተለይ በኦሮሚያ ክልል ይታያል። ሁሉም ማለት ይቻላል ሽንፈትን ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም። ከምርጫው በኋላ ፓርቲዎች ምን ሊሉ እንደሚችሉ አሁን የሚያደርጉትንና የሚናገሩትን ሰምቶ መገመቱ ቀላል ነው።

ካለፉት 5 ምርጫዎች ጋር የዘንድሮው ሲነጻጸር ምን ይመስላል?
ለእኔ ብዙ የተለየ ነገር የለውም። ህወሓቶች፣ ምርጫ የዓለምን ጆሮ ይስባል ብለው ስለሚያስቡ ዲሞክራሲያዊ ነን ለማለት ብቻ ይፈልጉት ነበር። ከምርጫው በፊት ጥሩ ነገሮችን ያደርጉና በኋላ ላይ ግን የሕዝብን ድምፅ ቀልብሰው እንደሚወስዱ የምናውቀው ነው። አሁንም በዚህ ምርጫ ለመፍጠር የተፈለገ ገጽታ አለ። ፖለቲካዊ ቅቡልነት ከማግኘት የዘለለ ጥቅም የለውም። የአሁኑን የሚለየውና የባሰ የሚያደርገው ደግሞ አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗ ነው። በቀድሞዎቹ አንጻራዊ መረጋጋት ነበር። አሁን በተቃራኒው ያለ፣ እርስ በርሱ የተተራመሰና ቀውስን የመፍታት አቅም ዝቅተኛ በሆነበት ጊዜ የሚደረግ ምርጫ መሆኑ ከቀደሙት የባሰ ያስብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here