“በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት የተጀመረው የግድቡ ድርድር መቀጠል አለበት” ሩሲያ

0
713

በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት የተጀመረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሩሲያ አስታወቀች። የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በሞስኮ ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፣ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት በተጀመረበት አግባብ መቀጠል እንዳለበት አገራቸው ጽኑ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል። ለዚህም ሩሲያ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል ብሏል ጽህፈት ቤቱ።
አቶ ደመቀ፣ መንግስታቸው በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን የመልሶ ግንባታ እና ሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከተ ለሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ መስጠታቸውም ተገልጿል። ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል በኃላፊነት የወሰዳቸው እርምጃዎች እና በቁርጠኝነት የሚያከናውናቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት የመንግስትን የሞራል ጽናት እና የፖለቲካ ብቃት ማሳያ ናቸው” ማለታቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ግጭት በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር እና ችግሮችን በዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት የምትከተለውን ጤናማ አካሄድ እንደምታደንቅም ሰርጌ ላቭሮቭ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረገውን ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት ሩሲያ እንደማትደግፍ የገለጹት ሰርጌ ላቭሮቭ፣ በኹለቱ አገሮች መካከል ያሉ የትብብር መስኮች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here