የመስኖ ልማት ኮሚሽን በ4 ቢሊዮን ብር ወጪ የከርሰ ምድር ውኃ በመጠቀም የመስኖ ልማትና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ለማከናወን ‹ሩራል ኮሚዩኒቲ ኮርፖሬሽን› ከተባለ የኮሪያ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራረመ። በኦሮሚያ ክልል አደአ በቾ ላይ የሚገነባው ፕሮጀክት አምስት ሺሕ ሄክታር መሬት ከከርሰ ምድር በሚገኝ ውኃ በመስኖ በማልማት ሃያ ሺሕ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያና የኮሪያ መንግሥታት በገቡት የፋይናንስ አቅርቦት ስምምነት የሚገነባ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ከመስኖ ልማት ባለፈ ለአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለጤና ተቋማትና ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡ በመጪዎቹ 12 ወራት የፕሮጀክቱ ዝርዝር ጥናትና ዲዛይን የሚከናወን ሲሆን፣ በቀጣዩ አንድ ዓመትም ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሏል። ግንባታው 42 ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮና ቀደም ሲል የተቆፈሩ ጉድጓዶችን የማጎልበት ሥራን ያካትታል። ፕሮጀክቱ ግብርናውን የሚያዘምን፣ በምርቶች ላይ እሴት መጨመር የሚያስችልና በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው ኮሪያዊያን የእውቀት ሽግግር የሚያስገኝ ነው ተብሏል። የአካባቢውን ነዋሪዎች ሕይወት የሚቀይር፣ በአዲስ አበባ የሚታየውን የአትክልትና ፍራፍሬ እጥረት የሚቀርፍ፣ ደረጃውን የጠበቀ ምርትም ለመዲናዋ ማቅረብ የሚያስችል እንደሆነም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013


