6ተኛው አገራዊ ምርጫ ከረጅም ጊዜ ጥበቃ በኋላ በያዝነው ሳምንት ይካሄድባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች በአብዛኛው ተካሂዷል። ከምርጫው በፊት የነበሩ ችግሮችን ማሻሻል ባልተቻለባቸው ቦታዎች ምርጫው ለጳጉሜ እየተሸጋገረ ሰኔ 14 ቢደርስም፣ በርካታ ያልተጠበቁ ክስተቶችን አስተናግዷል። እስከዛሬ በኢትዮጵያ ከተደረጉ ምርጫዎች ውዱ ነው የተባለለት ይህ ምርጫ በቁሳቁስ አቅርቦትም ሆነ ዘመናዊነት የተሻለ ነው ቢባልም፣ በዝግጅት ማነስ ይሁን በእኩያን ተግባር ግልጽ ባይደረግም፣ በዋናዋ ከተማ አዲስ አበባ ጭምር ችግር ተፈጥሮበት ነበር። ችግሩ በርካቶች ለሰዓታት ቆመው እስከ ሌሊት ድረስ እንዲመርጡ አስገድዷል። ምርጫ አስፈጻሚዎችም እዛው ለማደር ተገደዋል።
ዘንድሮ ከተስተዋለው የምርጫ እንከን አንዱ የመራጩ ግንዛቤ አለመኖር ይጠቀሳል። በአዲስ አበባ ሳይቀር የአመራረጥ ሂደቱን ባለመረዳት ከተፈቀደው ውጭ የመረጡ፣ ጭራሽም ሳይመርጡ ኮሮጆው ውስጥ የከተቱ መኖራቸውን በቆጠራው ሂደት ለመታዘብ ተችሏል። አዲስ ማለዳ አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን ለመከታተል ከዋናዋ ከተማ በተጨማሪ በክፍለ-ሀገርም ጋዜጠኞችን አሰማርታ ነበር።
በክልል ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች የምርጫ ሂደቱ ምን እንደሚመስል ለመመልከት ከተመረጡት ከተሞች አንዷ ደብረ ብርሃን ናት። በምርጫው ዋዜማ ከተማዋ የተገኘነው ጋዜጠኞች ወደተለያዩ ቀበሌዎች በማምራት ምርጫ ጣቢያዎችን አይተናል። በ 2 የከተማው ቀበሌዎችና በአንድ የገጠር ቀበሌ የሚገኙ 18 ምርጫ ጣቢያዎችን በመለየት በተወሰኑት ውስጥ እየገባን የዋዜማው ዝግጅት ምን እንደሚመስል ተመልክተናል። ከምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎችና የፀጥታ ኃይሎች፣ እንዲሁም ምግብ አብሳዮች ዝግጅት በተጨማሪ ሕዝቡስ ምን ያህል ዝግጁ ነው የሚለውን ለማወቅ ዳሰሳ አድርገናል። በየቡድን ሆነው ስለምርጫው ያላቸውን አስተያየት፣ ስለፓርቲዎች አይነትና ይዘት ከሚያወሩት ውጭ፣ ደፈር ብለው ከማያውቁት እንግዳ ሰው ጋር ስለምርጫው ለማውራት ፈቃደኛ የሚሆኑ ለማግኘት ከባድ ነበር። ፍርሃት እንዳለ ከሚያሳብቀው ከነዋሪው ባህርይ በተጨማሪ አለመተማመን መኖሩ በግልጽ ተስተውሏል። አልፎ አልፎ በመኪና ተጭነው ከሚያልፉ የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች ውጭ ከወትሮው የተለየ ነገር እንደሌለ አንዳንዶች ነግረውናል። ምሽቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታዮች ጾም የሚይዙበት እንደመሆኑ ከሌላው መሰል ቀን በተለየ መጠነኛ ግርግር መኖሩን የጠቆሙንም ነበሩ። ይህ ቢሆንም ግን የምርጫ ዋዜማ እንደመሆኑ ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡ በጊዜ ወደየቤቱ እንደተከተተ ለመረዳት ችለናል።
በምርጫው ቀን ከንጋቱ 11፡45 ላይ በአንደኛው ምርጫ ጣቢያ ስንገኝ በርካቶች ተሰልፈው ረጅም ሰልፍ ጠብቆናል። ውስጥ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ሲዘገጃጁ ደርሰን 12 ሰአት እንዳለፈ የምርጫ ሂደቱ ተጀምሯል። በልምድ ማነስም ሆነ በጊዜ እጥረት ሳቢያ አንዳንድ መስተጓጎሎች እየተፈጠሩ ሂደቱ ሊፈጥን ባይችልም፣ ግርግሩ እስከ ከሰአት ቀጥሎ ነበር። በአንድ ግቢ እስከ 8 ምርጫ ጣቢያዎች የተዘጋጁበት ሁኔታ ስለነበር ለረጅም ሰልፍና ግፊያ ዳርጎ ነበር። መጨረሻ ተሰልፈው የነበሩ በአማካይ ኹለት ሰአት ፈጅቶባቸው መምረጫ ጣቢያቸው ጋር ለመድረስ መቻላቸውን ለማወቅ ችለናል።
ምርጫው እየተካሄደ ሳለ ቀስ በቀስ ያልተጠበቁ አከራካሪ ጉዳዮች እየተፈጠሩ ለቃላት ምልልስ ዳርገዋል። ፖሊስ ተጠርቶ ሰልፍ ላይ የነበረውን ትፍግፍግ አስቀርቶ በስርአት እንዲሰለፉ ማድረግ ቢችልም፣ ርቀትን ማስጠበቅ ሳይቻል ግን ቀርቷል። በአንዱ ቀበሌ ሴትና ወንዱን ለፍተሻ እንዲመች በሚል ለየብቻ አሰልፈው ትርምሱን በአንጻራዊነት ለመቀነስ አስችሏቸዋል።
በዕለቱ መራጮችን ካወዛገበው ጉዳይ መካከል ያለመታወቂያ እንምረጥ ያሉትን የተመለከተው አንዱ ነው። ሕብረተሰቡ ስለምርጫው ሕግ ካለማወቁ የተነሳ የተነገረውን ከመፈጸም ውጭ ሲያንገራግር አይታይም። ካርዱ ይበቃል ብለው ያለመታወቂያ የመጡትም ሆኑ የረሱ እንዲመለሱ ሲደረጉ ለምን ይቻላል ብለው አጥብቀው የተከራከሩ አንድ እናትን አግኝተናል። ከምርጫ ኃላፊው ጋር የነበረው ክርክር እልባት ባለማግኘቱ ወደ ጥሪ ማዕከል ደውለው እንደማይቻል ቢናገሩም፣ ጉዳዩን የሰማ አንድ ታዛቢ በተቃራኒው ሲሞግታቸው ድጋሚ ደውለው ሌላ ሰው እንዳገኙና ጠብቁ ተብለው ከቆይታ በኋላ ምላሽ ተገኝቷል። ካርዱ ላይ የተመዘገበው ስም የእነሱ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ሌላ አይነት መታወቂያ ካላመጡ እንደማይቻል ተነግሮ፣ ለማምጣት ወደቤታቸው እንዲመለሱና በድጋሚ ያንን ረጅም ወረፋ እንዲሰለፉ ተደርገዋል።
ሌላው መራጩን ግራ ያጋባው ኹለት የምርጫ ወረቀት ላይ የተለያየ ቁጥር ምረጡ የመባሉ ጉዳይ ነው። የትኛው ላይ ስንት ሰው እንደሚመርጡ ቢነገራቸውም ሕዝቡ ግራ እየተጋባ ሲመርጥ ታይቷል። ስለአመራረጡ የማስተማሩ ሂደት ከጣቢያ ጣቢያ በከፍተኛ መጠን የሚለያይ ሲሆን፣ አንዳንዴ እየተረሳ ግራ ሲጋቡ ሲጠይቁም አስተውለናል። ወረቀቱ ተሰጥቷቸው ምንም ምልክት ሳያደርጉ የሚከቱ በርካቶች እንደነበሩ በቆጠራው ሂደት የተረጋገጠ ነበር። አንድ አባት እንደተሰጣቸው ወዲያው ኮሮጆው ውስጥ ሊከቱ ሲሉ ስለታዩ በርብርብ እንዲመርጡ ቢነገራቸውም ሊገባቸው ስላልቻለ፣ አንድ ሌላ ሚስታቸውን ሊረዱ አስፈቅደው የገቡ አዛውንት እኔ እረዳለሁ ብለው አስመርጠዋቸዋል። እንዲህ የማያውቁትን የተባበሩት አባት ግን የሚስታቸው ተራ ሲደርስ ሌላ ሰው መርዳት አይችሉም ተብለው በሀዘኔታ እንዲመለሱ ተደርጓል። ባለቤታቸውን የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚ መከለያው ውስጥ አስገብቶ ከብዙ ደቂቃዎች የማስረዳት ሂደት በኋላ ወረቀታቸውን ኮሮጆው ውስጥ አስገብቶላቸዋል። ረዳትን በተመለከተ አካል ጉዳተኞች የራሳቸውን እየያዙ በመምጣት ቢመርጡም፣ ራሳቸው የሚችሉ ግን ሁኔታዎች እንዳልተመቻቹላቸው አይተናል። መቆም ለማይችሉ ተሸፍነው የሚያስደግፉበትና የሚመርጡበት መከለያ አለመኖሩ አንዱ የታዘብነው ጉዳይ ሲሆን፣ ኮሮጆው ላይ ለመድረስ ባለመቻላቸው መሬት በማድረግ ለማመቻቸት አስፈጻሚዎቹ ሲጥሩ አይተናል።
በሌላ በኩል መራጮች ምልክት ካደረጉ በኋላ የትኛውን የትኛው ኮሮጆ ውስጥ እንደሚያስገቡ ሲቸገሩ አይተናል። የአስፈጻሚ እጥረት ባለባቸው ጣቢያዎች በተለይ ሥራ እየበዛባቸው ስህተቶች ተፈጽመዋል። ይህ በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል ሲሆን፣ ሳጥኑ ሲከፈት የአንዱን ወደ አንዱ በመመለስ የተስተካከለ ነው። በአንድ ጣቢያ ኮሮጆ ውስጥ ያልገባ መከለያ ሳጥኑ ውስጥ የተሸጎጠ የምርጫ ወረቀት ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ተገኝቶ በስምምነት እንዲቀላቀል ተደርጓል። ይህ የሚያሳየው አንድ ሰው ምልክት አድርጎ ሲወጣ ስለመክተት አለመክተቱ የሚከታተለው አለመኖሩን ።
ሕብረተሰቡ ስለምርጫው ሂደት ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሚባክነው ድምጽና ሀብት ብዙ ነው። ከኹሉም በርካታው ስህተት መምረጥ ያለባቸውን ቁጥር ያለማወቅ ነገር ነው። አንዳንዶች ለተወካዮች ምክር ቤት መምረጥ የነበረባቸውን አንድ ሰው ለክልል እያደረጉ በማዘበራረቅ ከሚፈለገው በላይ የመረጡበትና ድምጻቻ ውድቅ ሲሆንና ተጨማሪ የመምረጥ እድላቸው ሲባክን አይተናል። ከተፈቀደው በላይ ኹሉንም የሚመርጡና ሙሉ ወረቀቱ ላይ የኤክስ ምልክት ያደረጉም ነበሩ። ጭራሽ ሳይመርጡ ባዶ ወረቀት የሚያስገቡም በርካታ ነበሩ። ከሳጥኑ ውጭ የተወዳዳሪዎች አርማ ላይ ምልክት ያደረጉም ነበሩ። ከታዛቢዎች ቅሬታ ቢያስነሳም አሻሚ እስካልሆነ ተቀባይነት እንደሚኖረው በመነገሩ ችግሩ ወዲያው ሲፈታ ተመልክተናል። ድምጽ በመስጠቱ ሂደት መከለያው ውስጥ አልገባም ብለው ያስቸገሩ አንድ እናትም አጋጥመው ነበር። ለምስጢራዊነቱ ተብሎ ተደብቀው እንዲመርጡ ቢነገራቸውም ማንንም አልፈራም ፊት ለፊት እመርጣለሁ ቢሉም በግድ ተሸፈኑ መባላቸው ልዩ አጋጣሚ ነበር።
በአንድ ጣቢያ ከተመዘገቡ1070 መራጮች በዕለቱ ከሩብ በላይ ሳይመርጡ ቀርተዋል። ከመረጡት 750 ሰዎች 80 ወረቀቶች ድምፅ አልባ እንዲሆኑ የተበላሹ ተብለው ተመዝግበዋል። ለተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡ 6 ዕጩዎች የተሰጠው ድምጽ በጊዜያዊነት ሲቆጠር ድምሩ 740 ወረቀት ሆኗል። 10ሩ የት እንደገቡ ባይታወቅም፣ ታዛቢዎችም እየተቀያየሩ የአንድ ፓርቲን ድምጽ ብዛት ሦስት ጊዜ ቢቆጥሩም፣ ሦስቱም የተለያየ ቁጥር በመናገራቸው እንዲቆይ ተደርጎ ነበር።
መራጩ ሕብረተሰብ በድራማ መልክም ይሁን በማስታወቂያ ተምሮ እንዴት መምረጥ እንዳለበት ስላላወቀ ተራው ሲደርሰ ሲጨነቅና ሲደናበር ይታይ ነበር። ፊደል መቁጠር የሚችለውም ጭምር ሲደናገርና አስፈጻሚዎቹ ላይ ሥራ ሲያበዛ ታይቷል። ከተመለከትናቸው 18 ጣቢያዎች በአንዱ ብቻ አንድ ምርጫ አስፈጻሚ ውጭ የተለጠፈ ፖስተርን ተጠቅሞ በአግባቡ ሲያስተምር ተመልክተናል።
በድምጽ አሰጣጡ ሂደት ከተስተዋለው የመራጩ ግንዛቤ ማጣት በተጨማሪ፣ በቆጠራው ወቅት የተመለከትናቸው ማስረጃዎች ምን ያህል የግንዛቤ ማጣት እንደነበረ አመላካች ናቸው። ማንን እንደሚመርጡና ምልክቱ ምን እንደሆነ ጭራሹኑ የማያውቁ እናትም ለመረዳት አስቸግረው እንደነበረም ሰምተናል። ምረጡ ስለተባሉ ብቻ ገበያ ወጥቶ እህል እንደመግዛት መስሏቸው የተከሰቱ ነበሩ። ሳያውቁ መምረጥ ከባድ ከመሆኑ አንጻር ይህን የመሳሰሉ ክስተቶች በዋናዋ ከተማ ጭምር መከሰቱን የሚናገሩ አሉ።
ከከተማ ወጣ ሲባል ነገሩ የባሰ ይሆናል። እነዚህን ምረጡ እያሉ ያስገድዳሉ፣ ያታልላሉ፣ ተፅዕኖም ይፈጥራሉ ለሚሉ ስሞታዎች መነሻው የመራጭ ግንዛቤና እውቀት አነስተኛ መሆኑ እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም። ቅድሚያ ማስተማር ላይ ፓርቲዎችም ሆኑ ምርጫ ቦርድ በሰፊው ባለመሥራታቸው ችግሩ መከሰቱን መገመት አይከብድም። ጮሌ የተባለች የገጠር ቀበሌ ውስጥ የታዘብነው ተመሳሳይ ነገር ነው። በግብርና የሚተዳደሩ መራጮች እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው ሳይረዱ ጣቢያው በመገኘታቸው ምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ትልቅ ጫና ፈጥረው ነበር። በአጠቃላይ ሕብረተሰቡ እንዴት እንደሚመርጥ መብትና ግዴታው ምን እንሆነ አስቀድሞ አለማወቁን ለመገንዘብ ችለናል።
ምርጫው በድሃ አገር አቅም ትልቅ የሚባል ወጪ ወጥቶበት በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ለኪሳራ መዳረግ የለበትም። በአስፈጻሚዎችም ሆነ በመራጮች ግንዛቤ ማነስ ሳቢያ የብዙዎች ልፋትና ጥረት መና መቅረትም የለበትም። በዚህኛው ምርጫ በሁሉም በኩል የተስተዋሉ ድክመቶችና ችግሮች ተጠንተው ለቀጣይ ምርጫዎች መሻሻል እንደግብዓት መማሪያ ሊሆኑ ይገባል። “አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” እንደሚባለው ሳያውቅ የሚመርጥ ቀለም ከመለቅለቅ ያለፈ ሚና ሊኖረው ስለማይችል፣ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲኖረን መስራት ይገባል።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013



