ምርጫው በጥሩ ሁኔታ መካሄዱን የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ገለጸ

0
572

ኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ ያካሄደችው ጠቅላላ ምርጫ በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች የተረጋጋና ሰላማዊ ድባብ ተላብሶ መካሄዱን መታዘብ ችያለሁ ሲል የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምርጫ ታዛቢ ቡድን ገለጸ።
ቡድኑ ትናንት በአራት ክልሎችና በኹለት ከተማ አስተዳደሮች በ190 የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ የምርጫውን ሂደት መታዘቡን ገልጿል። በዚህ መሰረት ባወጣው የመጀመሪያ ሪፖርት ከምርጫ ጣቢያዎች በወቅቱ መከፈት፣ የምርጫ ሂደት፣ የመዝጊያና ቆጠራን ማዕከል አድርጎ ባደረገው የመታዘብ እንቅስቃሴ የምርጫ ሂደቱ በአመዛኙ ሰላማዊ ሁኔታን የተላበሰ እንደነበር ገልጿል።
የምርጫ ታዘቢ ቡድኑ ኃላፊ አምባሳደር አብዱላሂ አውላ አሊ እንደገለጹት፣ ሂደቱ በጠንካራ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ የታጀበ፣ ንቁ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተሳትፎ የታየበት ነበር። የምርጫ ጣቢያዎች በወቅቱ የመከፈት ሂደቱም ቡድኑ ከተመለከታቸው ጣቢያዎች 81 በመቶ የሚሆኑት በታቀደው ሰዓት መሠረት የተከፈቱ ናቸው ብለዋል።
የምርጫው ቁሳቁስ ሥርጭቱም በአመዛኙ በቂ ቢሆንም የተወሰነ እጥረት ማጋጠሙን መታዘባቸውንም ጠቁመዋል። “የተሻለ የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ መታየቱ የሚበረታታ ተግባር ነበር” ብለዋል። በጥቅሉ በቡድኑ ቅኝት በተደረገባቸው አካባቢዎች አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ በሰላማዊ ድባብ ውስጥ ሆኖ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። ከመራጮች ብዛት ጋር ተያይዞም የተደረገው የሰዓት ጭማሪ ውሳኔ ሚዛናዊነት የተላበሰ እንደነበረም አንስተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here