በመኝታ ክፍላቸው ሞተው የተገኙት ጆን ማርሽ የምርጫው ልዩ እንግዳ እንጂ ታዛቢ አለመሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ የካርተር ማዕከልን በመወከል በምርጫው የተገኙ ዓለም አቀፍ ታዛቢ ናቸው መባሉን አስተባብሏል።
የምርጫውንና የቆጠራ ሂደቶችን በማስመልከት መግለጫን የሰጡት የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ “ግለሰቡ በእርግጥ በታዛቢነት ሳይሆን ድጋፍ እንደሚሰጡ እንደ ማንኛውም ዓለም አቀፍ ተቋም በእንግድነት (as a gust) ነው ከእኛ (ቦርዱ) ባጅ የወሰዱት” ሲሉ ተናግረዋል።
የልዩ እንግዳ ባጅ በተለያየ ሁኔታ የምርጫውን ሂደት የሚከታተሉ ነገር ግን የመታዘብን ሥራ ለማይሰሩ አካላት፣ ከአጋር ድርጅቶች፣ ከኤምባሲዎች ከመሳሰሉት የሚሰጥ ባጅ ነውም ብለዋል ኮሚዩኒኬሽን አማካሪዋ።
ስለዚህ ካርተር ማዕከል ታዛቢም የለውም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመታዘብም ተልዕኮ የመጣ የላቸውም ነው ያሉት። ሆኖም ጆን ማርሽ እንደ ግለሰብ ድርጅቱን ወክለው የምርጫውን ሂደት ለማየት መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
የማዕከሉ የአዲስ አበባ አስተባባሪ መሆናቸው የተነገረላቸው የጆን ማርሽ የአሟሟት ሁኔት ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር እየተጣራ ነው መባሉ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013



