አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫቸው ኢትዮጵያ 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በሰላምና ሂደቱን በጠበቀ መልኩ ማከናወኗን ለዓለም አሳይታለች ብለዋል።
አንዳንድ አካላት ምርጫውን ተከትሎ በኢትዮጵያ ግጭቶች ይኖራሉ የሚል ትንበያና ምኞት ቢኖራቸውም ሕዝቡ የሚያኮራ ሰላማዊ ምርጫ ማካሄዱን ተናግረዋል።
በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች መራጩ ሕዝብ ድምጽ መስጠት ከተጀመረበት ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ተሰልፎ በትዕግስት ድምጹን መስጠቱን ገልጸዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ምርጫው ሰላማዊ፣ ቅደም ተከተላዊ፣ ሥርዓቱን የተከተለና ተዓማኒ መሆኑ በአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መገለጹንም ለአብነት አንስተዋል።
ስለዚህም ምርጫው ለሌሎች የዓለም አገራት ምሳሌ መሆን በሚችል መልኩ መጠናቀቁን ነው ያወሱት።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013



