የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሰኔ 14/2013 የተካሄደውን ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
ኢዜማ በመግለጫው መጀመሪያ ላይ ምርጫው በብዙ ችግሮች የታጀበ ነበር ብሏል። ፓርቲው በምርጫው ላይ የተመለከታቸውን ከ460 በላይ ችግሮች ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ገልጿል። አንዳንዶቹ ግድፈቶች የምርጫውን ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው ብሏል። ከእነዚህም መካከል የኢዜማ ዕጩዎች ያልገቡባቸው የምርጫ ወረቀቶች መሰራጨታቸው የሚለው አንዱ ነው።
ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ ያቀረባቸው ችግሮች ምላሽ የማያገኙ ከሆነ ወደ ፍትህ አካላት እንደሚሄድ አስታውቋል። ይሁንና ፓርቲው የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ሳይሰማ የምርጫው ውጤት ላይ አቋም እንደማይዝ ተናግሯል።
ኢዜማ አቋም ከመያዙ በፊትም ተከታታይ ውይይት እና ግምገማዎችን እንደሚያካሂድ አስታውቋል።
ሰኔ 14/2013 የተደረገው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት እስከሚገለጽ የምንጠብቅ ሲሆን፣ ቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትና በየሰዓቱ ለምርጫ ቦርድ ያሳወቅናቸው በርካታ ተግዳሮቶችን በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካላት ይዘን የምንሄድበትን ሁኔታ ቀድመን ለሕዝብ እናሳውቃለን ብሏል።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013



