የ6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰኔ 14 ተካሂዶ አጠቃላይ ውጤቱ በመጠበቅ ላይ ይገኛል። ብዙ ወጪ የወጣበትና የተለፋበት የምርጫ ሂደት ከድምፅ መስጠቱ ሂደት በኋላ በርካታ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት እየተሰማ ነው። ከሰኔ 14 በፊትም የተለያዩ ስሞታዎችን ሲቀበል የነበረው ምርጫ ቦርድ ችግሮችን ለመፍታት በተቻለው ሲጥር ቆይቷል። ማስተካከል የተቻለውን እያረመ፣ በመንግስት በኩል መደረግ ያለበት እንዲፈጸም ግፊት በማድረግ እልባት ሲሰጥ መቆየቱን የተለያዩ ፓርቲዎች ጭምር እማኝነታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። አንዳንድ በቀላሉ መፍታት ያልቻላቸውን ችግሮች ይፋ በማድረግ የምርጫ ቀን እንዲሸጋገር ማድረጉም ይታወሳል።
ከፍተኛ ወጪ በማውጣት እርማትና ማሻሻያዎችን እያደረገ የምርጫው ቀን የደረሰበት ቦርዱ፣ ከዋዜማው ጀምሮ ውጥረት ውስጥ ገብቶ ነበር። ከአስፈጻሚዎቹ መቅረት ጀምሮ ‹እንዲህ እያደረጉ ነው› የሚሉ የተለያዩ ቅሬታዎችን ሲያስተናግድ ከርàል። የፓርቲዎች ቅሬታ በቀጣይ ቀናትም በመቀጠሉ ውጤቱ እየተጠበቀ ነው። ምርጫውን አስመልክቶ የሚቀርቡ ማናቸውም አይነት ቅሬታዎችም ሆኑ ጥቆማዎች የድህረ-ምርጫ ሂደቱ ሳይጓተት አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት እንደሚገባቸው አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
የፌደራል ፖሊስ ምርጫውን ለማደናቀፍ በተለያዩ ቦታዎች ሴራዎች ታቅደው እንደነበረ በመናገር ለማክሸፍ መቻሉን መግለጫ በመስጠት ለሕዝብ አሳውቋል። በሰሜን ጎንደር ምርጫ ጣቢያን ሲጠብቅ የነበረ የፖሊስ ባልደረባ መገደሉን ይፋ ያደረገው መንግስት፣ ግድያው በምርጫው ላይ ስላስከተላው ተጽዕኖ ሳያብራራ ቀርቷል። በምንጃር የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ካለፈ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አባል ተይዘው የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ቢነገርም፣ በተመሳሳይ መርሃቤቴ ሲቀሰቅሱ የነበሩ የገዢው ፓርቲ አባላት ስለመያዛቸው እንጂ ስለተቀጡት ቅጣት ምንም የተባለ ነገር የለም። ይህን መሰል ድርጊቶች መፈጸማቸው ብዙዎችን ባይገርምም፣ አንዳንድ ተፈጸሙ የተባሉት ግን የሚገርሙም የሚያሳዝኑም ነበሩ።
የፓርቲ ተወካይ የሆኑ ታዛቢዎች ላይ የተፈጸሙ የኃይል እርምጃዎች፣ ማስፈራራቶችና ጫናዎች ከቀረቡት ቅሬታዎች ቀዳሚዎቹ ነበሩ። የየአካባቢ ካድሬዎች ፈጸሙ የተባለው ተግባር ተጣርቶ እውነትነቱ ከተረጋገጠ የጳጉሜው ምርጫ ላይ እንዳይደገም አፋጣኝ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
የምርጫው ውጤት ላይ ለውጥ የሚያመጡ የቅሬታ አይነቶች ተለይተው ምርጫው እንደተራዘመባቸው አካባቢዎች ውጤቱም መነገሩ ሊራዘም ይገባል። የጥቆማዎቹና ስሞታዎቹ ይዘት፣ የሚያመጡት ለውጥ፣ የቀረቡበት አካባቢና ሁኔታ ከግምት ውስጥ ገብቶ መስተካከል የሚችሉት መለየት አለባቸው። መደገም ያለባቸው እንዲሁም መረጋገጥ ያለባቸው ትንንሽ የሚመስሉ ቅሬታዎች ቢኖሩም ባለመናቅ ለሀሜትም ሆነ ለጥርጣሬ በር እንዳይከፍቱ ተደርገው ምላሽ ማግኘት አለባቸው።
የምርጫውን ውጤት ሙሉ በሙሉ ለመቀበል መጀመሪያ ሂደቱ ሕጋዊ በሆነ መስፈርት ተቀባይነት ማግኘት እንዳለበት ይታመናል። ፓርቲዎችም ሲሉት እንደከረሙት ፍትሃዊ ምርጫ እስከሆነ ድረስ ላለመቀበል የሚደረግ ትንቅንቅ የበለጠ የሚያስገምትና ያለን ደጋፊም የሚያሳጣ ይሆናል። ከታማኝ ምንጭም ሆነ ከራሳቸው ታዛቢዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎች በአግባቡ መፈተሸ አለባቸው። ያልተገባ የውሸት ስሞታ የሚያቀርቡ ሆን ብለው የውጤቱን ተቀባይነት ለማሳጣት አስበው መሆኑ ከተረጋገጠ በሕግ ሊያስጠይቃቸው ስለሚችል፣ አይሆንም ብሎ ከመገመት አስቀድሞ በራስ በኩል ማጣራቱ ተገቢ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
የምርጫውን ተቀባይነት የሚያሳጡ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የቦርዱንም ሆነ የሠራተኞቹን ታማኝነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ ቅሬታዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል። እንደምርጫው ሂደት ሁሉ ቅሬታዎቹንም ለመፈተሸ አስፈላጊው የሠው ኃይልና በጀት ተመድቦ በአፋጣኝ ውሳኔ እንዲያገኝ መደረግ ይኖርበታል። ጊዜው በረፈደ ቁጥር ማስረጃ ለማግኘት አዳጋች ከመሆኑ ባሻገር፣ በሕዝብ አስተሳሰብና ሥነልቦና ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ከባድ ይሆናል። ለዚህ ወቅት ተብሎ የምርጫ ጉዳዮችን እንዲመለከት ተቋቁሟል የተባለውን የምርጫ ፍርድ ቤት በማጠናከርና አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ፈጣን በሚባል ለቅሬታዎች ኹሉ በተቻለ መጠን ምላሽ መስጠቱ ለኹሉም ወገን ይጠቅማል።
ከምርጫው ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ ቅሬታዎች ለሚመለከተው አካል በቀጥታ መቅረብ የነበረባቸው ቢሆንም፣ አንዳንዶች አውቀውም ይሁን ሳያውቁት በቀጥታ ለሕዝብ ይፋ አድረገዋል። ሕብረተሰቡ ቅሬታን እንጂ ማስተባበያውን ያን ያህል ስለማይከታተል መዘዙ ከባድ ነው የሚሆነው። ለምሳሌ ያህል በደሴ ከተማ በድምፅ መስጫ ወረቀቶች የተሞሉ 5 ኮሮጆዎች ተገኙ ተብሎ ከባድ ሀዘኔታ ፈጥሮ ነበር። አጠቃላይ ውጤቱን ውድቅ ሊያስደርግ የሚችል ይህ አይነት መረጃ በሕዝቡ ዘንድ ከተሰራጨ በኋላ ቅሬታው ማሻሻያ ተደርጎበታል።
5ቱ ሳጥኖች ሙሉ በሙሉ በምርጫ ቦርድ የማይታወቁ ሳይሆኑ፣ በጣቢያዎቹ ከተመዘገቡት በላይ መራጮች ድምፅ የሰጡባቸው ነው ተብሎ ቢሻሻልም ያን ያህል መረጃው አልተሰራጨም። ይህ የተሻሻለው ቅሬታም ቢሆን “ከየት መጡ?” የሚል ከባድ ጥያቄ የሚያጭር በመሆኑ አፋጣኝ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ በቶሎ ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበት የአዲስ ማለዳ እምነት ነው።
የምርጫው መጠናቀቅን ተከትሎ፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን አስቀድመው ይዘው የተገኙ መኖራቸውና መታሰራቸው ቢነገርም ይህ በቂ አይደለም። እንዴት እንዳገኙት፣ ለማን እየሰሩ እንደሆነ፤ ምርጫ ቦርድ ውስጥ ካለ ሰው ጋር ግንኙነት ስለመኖሩ፣ ዓላማቸው ምን ያህል ሰፊ እንደነበርና ሌሎች ቀጣይ ምርጫዎች ላይ ተፅዕኖ ሊያስከትሉ ስለመቻላቸው በአፋጣኝ ማጣራትና ሕዝቡን ወደአመኔታው መመለስ ያስፈልጋል። ሕብረተሰቡ በመንግሥትም ሆነ በገለልተኛ ተቋማት ላይ ሊኖረው የሚገባው አመኔታ ቀድሞ ከነበረው እየባሰ እንዳይሄድ ይህ አጋጣሚ ሊያመልጥ አይገባም።
በማኅበራዊ ድረ-ገጽ የሚቀርቡና በብዙዎች ዘንድ እየተንሸራሸሩ የሚገኙ ጥቆማዎች ግዴታ ሕጋዊ መስመሩን ተከትለው እስኪመጡ መጠበቅ የለበትም። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ስለሚወሰደው ወታደራዊ የሕግ ማስከበር እርምጃ የተሳሳተ መረጃ እንዳይናፈስ እያጣራ የሚያሳውቀው አይነት ግብረ-ኃይል ለምርጫውም ማቋቋም ያስፈልጋል። ለምሳሌ፣ የምርጫ ውጤት ማሳወቂያ ቅፅ ላይ ስርዝ ድልዝ ተፈጽሞ የአሸናፊው ውጤት ተቀይሯል የሚለው መጣራትና ግኝቱ ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት። በፑል ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ሲያስገባ የሚያሳይ ምስልም በተመሳሳይ መጣራት አለበት። ቦታውንና ሁኔታውን የሚያውቁ በድብቅም ቢሆን ማብራሪያውን በመስጠት ለሚያጣሩ አካላት መተባበር ይገባቸዋል። ወንጀሉንም የሚፈጽሙ መረጃ እንዳያጠፉና ማስረጃዎችን እንዳይሰውሩ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ቅሬታው፣ ጥቆማውና ምርመራው እንዲሁም የሚወሰደው እርምጃ ጊዜ ሳይሰጠው መደረግ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
በወላይታ የሚወዳደሩ የተለያዩ ፓርቲዎች በጋራ ሆነው ስለቅሬታቸው የሰጡት መግለጫም በጥንቃቄ ታይቶ አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኝ ይገባዋል። በሕዝብ መካከል አለመተማመንና ቁርሾን የሚፈጥሩ፣ በፓርቲዎችም ሆነ በታዛቢ ቡድኖች የሚቀርቡ ቅሬታዎችና ጥቆማዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ እሙን ነው። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ያደረጋቸው ዋና ዋና ያላቸው በምርጫው ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች ገለልተኛ ከሆነ ተቋም እንደመገኘታቸው እውነተኛነታቸው አጠራጣሪ አይሆንም። ተቋሙ በ12 ከፍሎ ያስቀመጣቸው እነዚህ ችግሮችን ቦርዱ ተመልክቶ ሊማርባቸው ይገባል። ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸውንና ከፍተኛ ግድፈቶች ያሉባቸውን ለይቶ ከውጤቱ በፊት ምን እንደሚደረግ ለሕዝብ ማሳወቅ ይገባዋል። “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንደሚባለው ቀላል የሚመስሉ ቅሬታዎችም ቢሆን ምርጫውን ሰርስረው ተቀባይነቱን እንዳይሰብሩበት ቦርዱትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ ሊሰጥባቸውና በሙሉ ኃይሉ ሊረባረብባቸው ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ጥሪ ታቀርባለች።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013


