ዝቅተኛ የደሞዝ መጠንን የሚወስን አዲስ አዋጅ መዘጋጀቱ ተገለጸ

0
1354

የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቀጣሪዎችን አነስተኛ የደሞዝ መጠን መወሰን የሚያስችል አዲስ አዋጅ ማዘጋጀቱን ገለጸ። አዋጁ ተቀጣሪዎች የሚቀጠሩበት ደሞዝ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ሲተያይ በጣም አነስተኛ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የዝቅተኛ ደሞዝ ስኬል ለማሻሻል የሚያስችል መሆኑን ደጀኔ በቀለ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሥራ ስምሪት እና ሥራ ገበያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተናግረዋል። የደሞዝ ስኬል ማስተካከያ የሚባለው ደሞዝን ከገበያ ጋር ለማቀራረብ የመንግሥትን እና የግል ድርጅቶች የመክፈል አቅምን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚደረግ ማሻሻያ ነው።

ዝቅተኛ የደሞዝ መጠንን ለመወሰን የሚያስችል የደሞዝ አወሳሰን ተቋም (ቦርድ) ተደራጅቶ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑ ነው የተገለጸው። በአገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ መሰረት የደሞዝ መጠን ለቀጣሪው እና ተቀጣሪው የተተወ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ደጀኔ፣ ሕጉ ውሳኔውን ለሁለቱ ወገን ቢተወውም በአገሪቱ ባለው ከፍተኛ የሥራ ፈላጊ ቁጥር እና አነስተኛ የቀጣሪ ብዛት የተነሳ ሠራተኛው በአሠሪው ተጽእኖ ስር እንዲወድቅ አድርጎታል ብለዋል።

ቦርዱ በጥናት የተደገፈ ዝቅተኛ የደሞዝ መጠንን ቢያቀርብም፣ በቀጣሪው ላይ ይህን ያህል ደሞዝ ክፈል የሚል ጫና አያደርግም። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሠሪና ሠራተኛ በመደራደር በሚያደርጉት የኹለትዮሽ ስምምነት መነሻነት የደሞዝ ጭማሪ የሚኖር ከሆነ ጣልቃ እንደማይገባ ገልጸዋል። ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን በተቀጣሪ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ የሚያስችል የደሞዝ አወሳሰን ቦርድ አደራጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት አቅዷል። ቦርዱ የተለያዩ ባለሙያዎችን በአባልነት የሚይዝ ሲሆን፣ በየጊዜው የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ዝቅተኛ የደሞዝ መስፈርት ያሰቀምጣል ተብሏል።

ወቅታዊ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም ይህን ለማድረግ የሚያስገድድ መሆኑ ተወስቷል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባቋቋመው ቦርድ የተሠራው ይህ አዲስ ረቂቅ አዋጅ፣ የተለያዩ የምዋዕለ-ነዋይ ፍሰትን ለማስፋፋት እና የተቀጣሪዎችን አነስተኛ የደሞዝ መጠን ከፍ እንዲል ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። ቦርዱ ይህን ሥራ የሚሠራው በአገሪቷ ላይ ያለውን የተለያየ የዋጋ ንረት ጥናት መነሻ በማድረግ እንደሆነም ታውቋል። በተጨማሪም ጥናት ካደረገ በኋላ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያስተዳድራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የግል ተቋማት ላይ ዝቅተኛ የደሞዝ ክፍያ የሚቀመጥበትን ሥርዓት ይዘረጋል።

ቦርዱ ያዘጋጀው ይህ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለመንግሥት የሚቀርብበት ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ የማጸደቅ ሥራ እንደሚሠሩ ደጀኔ ተናግረዋል። አዋጁ እንደጸደቀ የተቋቋመው ቦርድ ቀጥታ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፣ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ አዋጁን በፍጥነት ለማጸደቅ የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል። እንደ 2018/19 የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ መሰረት በከተማ ውስጥ ካሉ 20 ሚሊዮን ተቀጣሪዎች ውስጥ 7.5 ሚሊዮን ሠራተኞች አነስተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው ናቸው። እነዚህ 20 ሚሊዮን ተቀጣሪዎች በመንግሥት፣ በግል እና ራሳቸውን ቀጠረው ወይም በራሳቸው ንግድ የሚተዳደሩት እንደሆኑ መረጃው ያሳያል።

ከነዚህ 7.5 ሚሊዮን ውስጥ 177,381 የሚሆነው ሠራተኛ በወር ከ500 ብር በታች የሚከፈለው ሲሆን፣ 547,595 የሚሆነው ሠራተኛ ደግሞ ከ500 -1000 ብር ወርሃዊ ደሞዝ የሚያገኝ ነው። ከ7.5 ሚሊዮን ዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋዮች መካከል ትልቁ ከ6000 -7000 ብር የሚከፈለው ሲሆን፣ እነዚህም በቁጥር 70ሺሕ መሆናቸውን መረጃው ያሳያል። ከ7.5 ሚሊዮን ተቀጣሪዎች ውጪ ያሉት በመካከለኛ እና ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ2012 ሪፖርት ያሳያል።
በዚህም መሰረት ዝቅተኛ ደሞዝ፣ ማለትም ከ500 ብር በታች ፣የሚከፈላቸው በአንጻራዊነት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል። ዝቅተኛ የደሞዝ መጠንን ከፍ ማድረግ መቻሉ በዋናነት ለስደት የሚዳረጉ ግለሰቦችን ማዳን እንደሚያስችልም ደጀኔ ጠቁመዋል።

ደጀኔ እንደሚሉት፣ ሚኒስቴሩ የሠራተኞችን አቅም መገንባት ዋነኛ ተግባሩ ስለሆነ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር በመሥራት ሠራተኞች ለመብቶቻቸው እንዲሟቱ ያደርጋል ብለዋል። በተጨማሪም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ እስከታች ድረስ ባሉ ተቋማት የሠራተኛ ደህንነት ተቆጣጣሪ መኖራቸውን የጠቆሙት ደጀኔ፣ እነዚህ ተቆጣጣሪዎች ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ሕግ ያጸደቀውን የሠራተኞች ደረጃ መከበርና አለመከበር፣ እንዲሁም ሥራ ቦታ ላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን ይከታተላሉ ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here