የበረሃ አንበጣው በኦሮሚያ ክልል ስጋት ፈጥሯል
በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ምሥራቃዊ ክፍል እና በሱማሌ ክልል በኖጎቦ፣ በጃራር፣ በኤረርና በፋፋን ዞኖች የበረሃ አንበጣ እንቁላል እየተፈለፈለ መኆኑ ተገልጿል። በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ምሥራቃዊ ክፍል እና በምዕራብ ሱማሌ ክልል የበረሃ አንበጣ እንቁላል መፈልፈሉን ቀጥሏል ተብሏል። በምሥራቅ ሱማሌ ክልል የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በአየር ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ያለበትን ሁኔታ መለየት አልተቻለም ተብሏል። በኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ እየተፈለፈለ መሆኑን የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት የበረሃ አንበጣ መከላከል ነው።
ጅርጅቱ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ ሥርጭ መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ምስራቃዊ ባሌ ዞን እና በሱማሌ ክልል በተለይም በምዕራብ ዞኖች በአፍደር ፣ ኤረር ፣ ፋፋን ፣ ጃረር እና ኖጎብ ዞኖች የበረሃ አንበጣ እንቁላል በመጣልና ቀድሞ ተጥሎ የነበረው በመጎልመስ ላይ ነው ብሏል። ድረጅቱ በሪፖርቱ እንደገለጸው ከሆነ ምናልባትም በሱማሌ ክልል በሌሎች ወረዳዎች እና ዞኖች የበረሃ አንበጣ እንቁላል እየጣለ ሊሆን ይችላል ብሏል። በኢትዮጵያ አጎራባች አገሮች በተለይም ጅቡቲ ውስጥ የተፈለፈሉ የበረሃ አንበጦች እድገታቸውን ጨርሰው ለመብረር የሚስችላቸውን የቡድን ምስረታ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
በኦሮሚያ ክልል የበረሃ አንበጣ እንቁላል ሊጥል ይችላል ተብሎ በሚታሰብባቸው አካባቢዎች በተለይ በሱማሌ ክልል አዋሳኝ አከባቢ፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ አሰሳ እያደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጌቱ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ በስጋት የሚመለከታቸውና እስካሁን የበረሃ አንበጣው እንቁላል ጥሎ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ባለባቸው እንደ ባሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ አካባቢ የአሰሳ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጌቱ ጠቁመዋል።
የአንበጣ መንጋው እንቁላል ለመፈልፈል የሚመቸው ቦታ ላይ እንደሚያርፍ የጠቆሙት ጌቱ፣ እንቁላል ከፈለፈለም በኋላ በኬሚካል ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የቦታው ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት የማይቻልበት ሁኔታ አለ ብለዋል። የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ተከስቶ ማጥፋት ሳይቻል ከሦስት ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ የገለጹት ጌቱ፣ በሱማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የሚፈለፈለው የበረሃ አንበጣ ለኦሮሚያ ክልል ሥጋት መሆኑን ጠቁመዋል። በሱማሌ ክልል የሚፈለፈለው የበረሃ አንበጣ በክልሉ የሚመገበው ሰብል ስለማያገኝ በኦሮሚያ ክልል በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ስጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በሱማሌ ክልል ተፈልፍሎ ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀስ የበረሃ አንበጣ መንጋ በቀጥታ የሚያርፈው ሰብል ላይ መሆኑን የጠቆሙት ጌቱ፣ የበረሃ አንበጣን የመከላከል ሥራ በዋናነት የግብርና ሚኒስቴር በመሆኑ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት የበረሃ እንበጣ መከላከል በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ እና በሰሜን ምዕራብ ሶማሊያ ካሳለፍነው ግንቦት ጀምሮ ብዙ የበረሃ አንበጣ እንቁላል እየጣለ እንደሆነ ጠቁሟል። እስካሁን ድረስ በጥቂት ቦታዎች የታዩ ትናንሽ ኩብኩባዎች እየተፈጠሩ ነው።
ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው ከሆነ እንደ አዲስ እየታየ ያለው የበረሃ አንበጣ እርባታ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የአንበጣን ቁጥር የበለጠ የመጨመር ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ተሰግቷል። የበረሃ አንበጦች እንቁላል የጣሉበት ቦታ ተለይቶ የተፈለፈለውን እንቁላል እድገቱን መግታት ካልተቻለ፣ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ አዳዲስ ቦታዎች ላይ የበረሃ አንባጣ መስፋፋት ሊፈጠር እንደሚችል በሪፖርቱ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የጎለመሱ መንጋዎች ከጅቡቲ በስተደቡብ አይሻ አቅራቢያ እንቁላል እየጣሉ መሆናቸውን ሪፖርቱ ጠቁሞ፣ በምዕራብ ሱማሌ ክልል ኖጎብ ዞን የተከማቸው የበረሃ አንበጣ መንጋ የቡድን ምስረታ ሂደት ላይ መሆኑ ተመላክቷል። በኢትዮጵያ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ባሳለፍነው የምርት ዘመን 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በኦሮሚያ ክልል አሳጥቷል። አጠቃላይ ከዓመታዊ የግብርና ምርት ላይ ባለፈው የምርት ዘመን የስምንት በመቶ ቅናሽ አሳድሯል መባሉ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013



