አዲስ ማለዳ በአፋን ኦሮሞ እና በሶማሊኛ ቋንቋ መረጃ ማቅረብ ጀመረች

0
788

‹ዜና ከምንጩ› በሚል መሪ ቃል የተረጋገጡ መረጃዎች፣ በሳል ወቅታዊ ትንታኔዎች እንዲሁም በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎችን ለአንባቢያን ዘወትር ቅዳሜ በማቅረብ የምትታወቀው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ፥ በአፋን ኦሮሞ እና ሶማሊኛ ቋንቋ ከዛሬ ቅዳሜ፣ ሰኔ 19/2013 ጀምሮ ለሦስት ወራት የሙከራ ገፆችን ማቅረብ ጀመረች።

ኹለቱ ቋንቋዎች ከጋዜጣዋ አራት አራት ገጾች የተመደቡላቸው ሲሆን፣ ከአዲስ ማለዳ አማርኛ ጋር በአንድ ዕትም ተካትተው ይቀርባሉ። በቋንቋዎቹ የሚቀርቡ ይዘቶች በአማርኛ ከቀረቡ ዜናዎች እና ዓምዶች ተመረጠው የሚተረጉሙ እንደሚሆን ታውቋል።

የአዲስ ማለዳ አሳታሚ ቻምፒየን ኮሚውኒኬሽንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ታምራት አስታጥቄ፣ የአዲስ ማለዳ በሦስት ቋንቋዎች መረጃዎችን ለተደራሲያን ማቅረብ የመጀመሯን አንድምታውን በተመለከተ ‹‹አዲስ ማለዳ አዳጊ መገናኛ ብዙኀን ብትሆንም፥ በአፋን ኦሮሞ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሯ ለሌሎች ተመሳሳይ የመገናኛ ብዙኀን ዐይን ገላጭ ከመሆኑ ባሻገር፣ የተደራሽነት አድማሷን ማስፋቷን ያመለክታል። በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ ተጽዕኖዋን ለማስፋትም ጠቃሚ ነው›› ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ከተሞች ዘጋቢዎች በቋሚነት ተቀጥረው የሚዘግቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በትኩረት እየሠሩበት እንደሆነ የገለጹት ታምራት፣ በጊዜ ሒደትም በኹለቱም ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ራሳቸውን የቻሉ ጋዜጦች እንዲኖሩ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።

የጋዜጣ ስርጭት ውሱንነትን በተመለከተም ታምራት ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት፣ ችግሩ መኖሩን አምነው አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የተወሰነ ቁጥር በአዳማ፣ በጅማ፣ በባሌ ሮቤ እና ጅግጅጋ ከተሞች ለማሰራጨት ዝግጅት መጠናቀቁም የታወቀ ሲሆን፣ የጋዜጣ ስርጭቱን ውስንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በኹለቱ ቋንቋዎች የሚቀርቡ መረጃዎች በ www.addismaleda.com ድረ ገጽ ላይ ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል ሲሉም አክለዋል።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባርን በማክበር ወቅታዊ መረጃ ማቅረብ፣ ስልጡን የውይይት መድረክ መፍጠር፣ የዜጎች ድምጽ (ልሳን) በመሆን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊነት እንዲያብብ፣ የመብት ተጠያቂነት እንዲጎለብት ብሎም ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲዳብር የማገዝ ዝርዝር ዓላማዎች ይዛ የተቋቋመች ሲሆን፣ በእስከዛሬ ጉዞዋም ገለልተኝነቷን በተግባር አረጋግጣለች። አዲስ ማለዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኅትመት ብርሃን ከበቃችበት ሕዳር 8/2011 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ያለምንም መቆራረጥ 138ኛ ዕትም ላይ ደርሳለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here