በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን የሁሉንም ምርጫ ክልሎች ውጤት ይፋ ማድረግ አለመቻሉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምጫ ቦርድ ገለጸ። የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እንደገለጹት፣ በድምር መዘግየት፣ በትራንስፖርት ችግር እንዲሁም የፖለቲካ ፖርቲዎች አቤቱታ ባቀረቡባቸው የምርጫ ክልሎች ውጤት ወደ ማዕከል ተጠቃሎ አልደረሰም። በዚህም እስካሁን ምርጫ ከተደረገባቸው የምርጫ ክልሎች የ26ቱ ውጤት አለመድረሱን ተናግረዋል።
በጋምቤላ 2፣ በአፋር 7፣ በአዲስ አበባ 8፣ በኦሮሚያ 4፣ በአማራ 3፣ በደቡብ ክልል 2 የምርጫ ክልሎች ውጤቶች አለመድረሳቸውን ጠቅሰዋል። ለቦርዱ ውጤት አያድርሱ እንጂ ምርጫ ክልሎቹ በአካባቢያቸው የምርጫ ውጤት የተለጠፈ መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ምርጫ ክልል አንድ የግል ተወዳዳሪ “በምርጫ ወረቀቱ ላይ ስሜ አልተካተተም” በሚል ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት በማግኘቱ ቦርዱ ቅሬታው አሳማኝ መሆኑን አረጋግጦ ምርጫ እንዳይካሄድ ወስኖ እንደነበርም አንስተዋል።
የአካባቢ ማህበረሰብ ምርጫው መሰረዙን ባለመስማቱ በምርጫ ክልሉ ካሉት 139 ምርጫ ጣቢያዎች በ105ቱ ምርጫ መካሄዱ በመረጋገጡ ድምጹ እንዳይቆጠር የድምጽ መስጫ ወረቀቱ ታሽጎ እንዲቀመጥ ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም ቅሬታ አቅራቢው የግል ተወዳዳሪ ምርጫ ከተደረገ በኋላ “በእኔ ምክንያት ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የለበትም” በማለቱ ውጤቱ እንዲቆጠር ቦርዱ መወሰኑን ገልጸዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013


