የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በ6ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ውጤት አሰባሰብ ሂደት እና በሂደቱ ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። እስካሁንም በ160 ላይ የተለያዩ ፓርቲዎች የቅሬታ አቤቱታ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ምርጫው ከተካሄደባቸው 942 የህዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች እስካሁን የ618 ውጤት ወደ ማዕከል መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ሆኖም ከአቤቱታዎቹ ከፊሉ በተደራጀ መልኩ ስላልቀረቡ ይኸው ተስተካክሎ እንዲቀርብ ለፓርቲዎች ጥሪ መደረጉን ጠቅሰዋል። ፓርቲዎች ላቀረቡት ቅሬታ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ዛሬ ከፓርቲዎች ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
ነገ የፓርቲዎቹን አቤቱታዎች ማየት እንደሚጀመር እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ቦርዱ የተረጋገጡና ችግር የሌለባቸው ያላቸውን የተወሰኑ የምርጫ ውጤቶች ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በተጨማሪ እነዚሁ ውጤቶች በቦርዱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይም ይፋ እንደሚደረጉ ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013


