የፌደሬሽን ምክር ቤት በጀት እስካሁን በሕገመንግሥቱ መሠረት ጸድቆ አያውቅም ተባለ

0
788

የማሻሻያ ረቂቁ የመገንጠል መብትን የሚያስተናግድበት አንቀፅ አካቷል

በሕገመንግስቱ አንቀፅ 65 መሰረት የፌደሬሽን ምክር ቤት በጀት በተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ቢታዘዝም እስካሁን በሕጉ መሰረት አለመፅደቁ ተገለጸ። የፌደሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደተነገረው የምክር ቤቱ በጀትን በተመለከተ እስካሁን ይሰራበት የነበረው አሰራር ተገቢ ባለመሆኑ አዋጁን ማሻሻል እንዳስፈለገ ነው። ይህን የሕግ ጥሰት ለማስተካከል እንዳዲስ አዋጁን በማሻሻል ምክርቤቱ በጀቱን በተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቅ የሚያደርግ አንቀጽ መካተቱ በረቂቁ ላይ ተመላክቷል። ማሻሻያ አዋጁ ምክር ቤቱ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ ታስቦ መዘጋጀቱ የተነገረ ሲሆን፣ ተቋማዊ የአፈፃጸም ብቃቱን ለማሻሻል ጥናት አስጠንቶ ረቂቁ እንዲዘጋጅ መደረጉ ተጠቅሷል። ሕገመንግስታዊ ጥያቄን መርምሮ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችለውን መዋቅር ለመዘርጋት ተብሎ ማሻሻያው መዘጋጀቱም ተነግሯል።

በነባሩ አዋጅ ላይ የነበሩና የተሻሻሉ አንቀፆችን ረቂቁ በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፣ ጽህፈት ቤቱ የነበረበትን የአደረጃጀት ክፍተቶችን የሚሞላ ሐሳብ ተካቶበታል። የጽህፈት ቤቱን ስልጣንና ተግባርን በተመለከተ ማሻሻያ የተደረገ እንደሆነ በረቂቁ የተመላከተ ሲሆን፣ ተጨማሪ አደረጃጀት እንዲኖር መደረጉም ተጠቅሷል። የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞችን በተመለከተ በአስተባባሪ ኮሚቴ በሚወጣ የአስተዳደር መመሪያ መሰረት እንዲተዳደሩ በአዲሱ ረቂቅ ተደርጓል ተብሏል። ዳይሬክተሮችን በተመለከተ በፊት የነበረው አሰራር ባይገለጽም፣ በአዲሱ አዋጅ እንዳስፈላጊነቱ በትምሕርት ዝግጅታቸው መሰረት እንዲመደቡ የሚያደርግ አንቀፅ በአዲስ መልክ መካተቱ ተጠቁሟል።

የረቂቅ አዋጁ ዝርዝር ይፋ በተደረገበት ሰነድ ክፍል ሦስት ላይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል አንቀፅ 24 ተካቷል። መገንጠልን በተመለከተ ስለሚቀርብ ጥያቄ የሚመለከተው አንቀፅ 26 ያብራራል። በሕገመንግስቱ አንቀፅ 39(4)(ሀ) መሠረት ኹለት ሶስተኛ ድምፅ ከብሔር ብሔረሰቡ ምክር ቤት አግኝቶ በጽሁፍ ለጽህፈት ቤቱ የሚቀርበው ጥያቄ በሦስት አመት ውስጥ የጠየቀው አካል ሕዝበ ውሳኔ ይደራጃል ተብሏል። ይህን ሂደት ተከትሎ አብላቻ ድምጽ ከተገኘ የስልጣን ርክክብ ተደርጎ የንብረት ክፍፍል እንደሚደረግ ያትታል።

በአጠቃላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኹለት አዋጆች እንዲሻሻሉ የሚያደርግ ረቂቅ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል። ምክር ቤቱ እንዲሻሻሉ ረቂቅ ያዘጋጀላቸው ኹለቱ አዋጆች ለ20 ዓመት ያህል ሲገለገልባቸው የነበሩትን ነው። መተዳደሪያ አዋጅ 251/1993 እና የምክር ቤቱ የጽህፈት ቤት አዋጅ 556/2000 ናቸው። ሲሆን፣ የማሻሻያ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በፌዴሬሽን ምክርቤት ጉባኤ ቀርቦና ውይይት ተደርጎበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር ለመዘርዘር እና የጽ/ቤቱን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል በወጡት ኹለቱ ረቂቅ አዋጆች ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማካሄዱ ታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here