የፌዴሬሽን ምክርቤት ኹለት የተለያዩ አዋጆችን ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩ ተገለጸ። ምክር ቤቱ ያሻሻላቸው ኹለቱ አዋጆች ለ20 ዓመት ያህል ሲገለገልበት የነበረውን መተዳደሪያ አዋጅ 251/1993 እና የምክር ቤቱ የጽህፈት ቤት አዋጅ 556/2000 ሲሆን፣ የማሻሻያ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በፌዴሬሽን ምክርቤት ጉባኤ ቀርቦና ውይይት ተደርጎበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር ለመዘርዘር እና የጽ/ቤቱን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል በወጡ ኹለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የመጀመሪያው መተዳደሪያ አዋጅ 251/1993 እንዲሻሻል የተፈለገበት ዋና ዓላማ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ አዋጅ በመሆኑ እና አሠራር ላይ ክፍተት የፈጠረ እና የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ-መንግስታዊ መብቶችን በተገቢው መንገድ ለማስከበር አዳጋች በመሆኑ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕግ አማካሪ ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ካለችበት የለውጥ ጎዳና እንዲሁም አሁን እየቀረቡ ካሉ የሕዝብ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች አንጻር ምክር ቤቱ በሕገ-መንግስቱ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በቀልጣፋ እና ውጤታማ አካኋን ለመፈጸም ሲባል መሻሻሉን ዘለቀ ተናግረዋል። ከፍርድ ቤት ውጪ የሚነሱ አቤቱታዎች ሲቀርቡ የሚከተሉት የአቀራረብ ስርዓት፣ በአቤቱታ አቀባበል እና ምርመራ ላይ የመተግበር ችግር እየፈጠረ በመሆኑ በዚህ አዲሱ ረቂቅ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አንቀጽ ተኳቷል ተብሏል።
ይህ አዲሱ አዋጅ ከብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እና ከመንግሥት የሥልጣን ክፍፍል ጋር የተያያዙ ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄዎች በስተቀር፣ ሌሎች ክርክሮች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ መብቶች ተጠይቀው መቋጨት እንደሚገባቸው አካቷል። በነባሩ ሕግ ያልነበረ ሌላኛው ተግባር ምክርቤቱ የሚያያቸው የትርጉም ጉዳዮች በምርመራ ላይ ሆነው በተለይ በፍርድ ቤት ታይተው የመጡ ጉዳዮች ከውሳኔ በፊት ቢፈጸሙ ውሳኔው ዋጋ እንዳያጣ ጉዳዩን አግዶ ማቆየት አንዱ ተግባር እንዲሆን ተደርጓል።
ይህ አዲሱ አዋጅ የሕገ-መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች በፌደራሉ ቋንቋ፣ በክልል የሥራ ቋንቋ፣ እና በእንግሊዘኛ እንዲታተም አድርጓል። ይህ ደግሞ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዘቦች በሚገባቸው ቋንቋ ሕገ-መንግስታዊ የትርጉም ውሳኔዎች እንዲጠቀሙበት እንዲሁም ለተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ፣ በክልሎች መካከል አለመግባባቶችን ስለሚፈቱበት መንገድ፣የጋራ ገቢዎች አወሳሰን፣ በሕዝቦች መካከል እኩልነትና አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳበር ስለማድረግ፣ የፍተሐ-ብሔር ጉዳዮችን ስለመለየት እና ስለምርጫ ክልል አከላለል የተመለከቱ ጉዳዮች በአዲሱ አዋጅ ተካተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማስቻል የምክር ቤት ጽ/ቤቱ የተቋቋመበትን አዋጅ ቁጥር 556/2000 ማሻሻል እንዳስፈለገ ዘለቀ አብራርተዋል ። ዜጎች፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ማኅበረሰቦች የሚያቀርቡትን ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ መርምሮ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን መዋቅር ለመዘርጋት የምክር ቤቱን ጽ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ነው አማካሪው የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት ያስረዱት። የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባርን ለመዘርዘር በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወሰኑ አንቀጾች ለተጨማሪ ሕገ-መንገስታዊ ትርጉም የተጋለጡ በመሆናቸው ቢስተካከሉ ያሏቸውን ነጥቦች የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቡ ብርኪ በበኩላቸው በአዋጆቹ ላይ የተነሱ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ አዋጆቹ በአጭር ጊዜ ተስተካክለው መቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013


