አነቃቂ ዕጾችና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድኃኒቶች በሕገ-ወጥ መንገድ እየተሸጡ ነው ተባለ

የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ያልተፈቀዱ አነቃቂ መድኃኒቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ሲሸጡ አግኝቻለሁ ብሏል። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ መድኃኒት ቤቶች ያለ ሐኪም ማዘዣ መድኃኒቶችን እየሸጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል። ባለሥልጣኑ በ2013 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት እንዲህ አይነት ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ መድኃኒት ቤቶችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ቀላል እና ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ እንደነበር አስታውሷል።

ከውጭ አገር በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ እና አነቃቂ እየተባሉ የሚሸጡ መድኃኒቶችን አሁን ላይ ይዘው የሚገኙ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ መድኃኒት ቤቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ ምግብ እና መድኃኒት ጤና ክብካቤ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ታመነ አሜሞ ናቸው።

አክለውም ኹሉንም ወረዳዎች እና ክፍለ ከተማዎች ባቀፈ መልኩ ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ለሦስት ወራት የኦፕሬሽን ሥራ ተሠርቶ እንደነበር ገልጸው፣ መድኃኒት ቤቶችን ጨምሮ በርካታ የህክምና ተቋማት ላይ አነዚህ ችግሮች መስተዋላቸውን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት። ይሁን እንጂ በኹሉም ተቋማት እና መድኃኒት ቤቶች ላይ የማሸግ እርምጃ መውሰድ ስለማንችል ለሁሉም ትምህርት ሊሰጥ በሚችል መልኩ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና ከስህተታቸው እንዲማሩ ለማድረግ በማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ከውጭ አገራት የሚገቡ ጥራት እና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድኃኒቶች እና አነቃቂ ዕጾች ለመድኃኒት ቤቶች እየቀረቡ መሆናቸውም ታውቋል ብለዋል።

በዚህም ረገድ በተለያዩ ተቋማት ላይ ጉድለቶች የሚስተዋሉበት ሁኔታ እንዳለም ነው ያነሱት። ይህ ቢሆንም ግን ከአደንዛዥ እና አነቃቂ ዕጾች ጋር በተያያዘ ጠንካራ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል። አያይዘውም፣ በአገር ውስጥ እንዲገቡ ያልተፈቀዱ እነዚህን ዕጾች ጨምሮ፣ ከሐኪም ትዕዛዝ ውጪ የሚሸጡ መድሃኒቶች ላይ ትኩረት ባደረገ ጥናት በመታገዝ ችግሮችን ማዕከል ያደረገ የክትትል ሥራ ለመሥራት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አነቃቂ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች ለጎንዮሽ ጉዳት እንደሚዳረጉ የሕክምና ባለሙያው ዶ/ር አመዘነ ወልዴ ተናግረዋል። እንደ ምሳሌም በአሜሪካ ከስድስት ሰዎች አንዱ የአነቃቂ መድኃኒቶች ተጠቃሚዎ መሆኑን አንስተዋል። ሐኪሙ እንደተናገሩት ሰዎች የአነቃቂ መድኃኒቱን የሚወስዱት ድብርትን ፣ ጭንቀትንና የእንቅልፍ እጦትን ለመከላከል ነው። አክለውም እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመከላከል ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶች ለጎንዮሽ ጉዳቶች ከመዳረጋቸው ባለፈ ሰዎችን ለመድኃኒቱ ጥገኝነትና ሱሰኝነት ሊዳርጋቸው ይችላል ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም አነቃቂ መድኃኒቱን መጠቀም ከጀመሩ 10 ሰዎች ውስጥ ስምንቱ ለማቋረጥ እንደሚቸገሩ ስለጉዳዩ የተደረገን ጥናት ጠቅሰው የሚያስከትለውን ጉዳት አብራርተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here