በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ የተባለው የህወሓት ታጣቂ ቡድን ላይ ወታደራዊ የሕግ ማስከበር እርምጃ መወሰድ ከጀመረ ከስምንት ወራት በኋላ፣ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ መከላከያ ከመቐለና ከሌሎች የትግራይ ግዛቶች መውጣቱ በርካታ አስተያየቶችን አስተናግዷል። የውሳኔው ድንገተኛ መሆን ለብዙዎች ዱብእዳ ከመሆኑ በላይ መንግሥትንም ሆነ ጊዜያዊ አሥተዳደሩን አምነው በክልሉ የቆዩን የተለያዩ አካላት ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ የጣለ ነበር። ሸፍቶ ዱር ለዱር የሽምቅ ውጊያ ሲያካሂድ የነበረው ታጣቂ ኃይል፣ ‹‹ያልተወራረደ ሒሳብ እናወራርዳለን›› እያለ ሲዝት መቆየቱን እያስታወሱ ውሳኔው ለጥቃት ያጋለጠን ሴራ ነው በሚል ድርጊቱን እንደክህደት የቆጠሩትም አሉ።
የመንግሥት ውሳኔ እንደተባለው ለሳምንታት ታስቦበትም ይሁን አይሁን ጥቅምና ጉዳቱን ቦታው ከነበሩ የጦሩ ባልደረቦች በላይ የሚያውቀው ስለማይኖር እነሱን መስማቱ የተሻለ እንደሚሆን ይታመናል። በጦርነቱ መጀመሪያ ወራት የነበረው የውጊያ ሂደት መልኩን እየቀየረ አሳዳጅና ተሳዳጁ ከተቀያየረ፣ የሚዋጋው አካል ማንነትና ደጋፊዎቻቸው ካወዛገበ ሊጠየቅ የሚገባው፣ ‹‹ውሳኔው ታዲያ ለምን ይህን ያህል ዘገየ?›› የሚለው መሆን ይኖርበታል።
ያም ሆነ ይህ፣ የሚሞተው ኢትዮጵያዊ የሚገልም ኢትዮጵያዊ እንደመሆኑ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ታዞ ለሚሞተው ቅድሚያ ሊታሰብ ይገባል። መጀመሪያ ሰሞን እንደነበረው አይነት እንክብካቤና ክትትል ለሠራዊቱ አሁንም ሊደረግና ለተሰዉትም መታሰቢያ ሊቆም ይገባል። ለአገርም ሆነ ለሕዝባቸው ብለው የሚሰዉትን አስከሬናቸውን በክብር ማሳረፍ ባይቻል እንኳን፣ ቤተሰቦቻቸው ተገቢውን ክብር አግኝተው ስለከፈሉት መስዋዕትነት በወቅቱ መረጃውን ማግኘት እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ታምናለች። በዘመቻው የተሰዉ ቤተሰቦቻቸው የሚደጎሙበትና ልጆቻቸው ነፃ ትምህርት የሚያገኙበት ሁኔታም ሊመቻች ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስለጦሩ መውጣት በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ዘመቻውን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አሳክተናል እንጂ አልተሸነፍንም›› ብለዋል። ይህ ማለት ከተጠበቀው በላይ መስዋዕትነት አልተከፈለም ማለት እንዳልሆነ፣ በተለያየ በርካታ ቦታ በጦሩ ላይ ያልታጠቀ ነዋሪ ጭምር ሲፈጽመው የነበረን በርካታ የጭካኔ ተግባር አንስተው፣ በተዘዋዋሪ ለሕዝብ ተብሎ የተወሰደ እርምጃን የሚቃረንን በክልሉ የነበረውን ሁኔታ አሳውቀዋል። ለጦርነት የተሰለፈ መሞት እንደሚኖር ቢያውቅም፣ እጠብቀዋለሁ እዋጋለታለሁ ባለው የሕዝብ አካል እንደተባለው ከጀርባ ተወግቶ ከሆነ የሠራዊቱ አባል ላይ ብቻ ሳይሆን ሌላው ቤተሰብና ዘመድ ላይ የሚያስከትለው የሥነልቦና ተጽዕኖና ሊፈጥር የሚችለው የቂም በቀል አስተሳሰብ በሁሉም ወገን ሊታሰብበት ግድ ይላል። ለጥቃት ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች የጦሩ አባላት ለጊዜው መራቃቸው ቢነገርም፣ ለጠላት እንዳይመቸው የት እንደሰፈሩ ይፋ አልተደረገም። በሌሎች ባልደረቦቻቸው ላይ የሚፈጥረው ስሜትም ከባድ ስለሚሆን፣ ከክልሉ ውጭ ባሉ አድፍጠው በሚጠብቁ የቡድኑ ደጋፊና ተባባሪ አካላት ላይ ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጠር እንደሚችል ሊጤን ይገባል።
በሌላ በኩል፣ የትግራይ ጉዳይ እንደአገር አሁንም አንገብጋቢ ቢሆንም ከእሱ የሚበልጥ፣ ልዩ ትኩረት የሚሻ፣ የመንግሥትን አቅም በቅድሚያ የሚፈልግ ጉዳይ መኖሩ ተነግሯል። ሳትጋበዝ ድንበር አልፋ የገባችው ሱዳንን የተመለከተ ሊሆን እንደሚችል የብዙዎች ግምት ቢሆንም፣ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ገበሬዎች እነሱም አርሰው ለመብላት እንዲችሉ መሬታቸውን መንግሥት ሊያስመልስላቸው እንደሚገባ እሙን ነው። መንግሥት ፊቱን ወደ አንገብጋቢው ጉዳይ ሲያዞር ሰርጎገቦች ዘልቀው እክል እንዳይፈጥሩ ቢደረግ መልካም ነው። በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል በኹሉም አቅጣጫ ተዘግቶባቸዋል ተብሎ፣ ከኤርትራ፣ አፋርና አማራ ክልል ጋር በሚዋሰኑበት፣ እንዲሁም የማይዋሰኑት የሱዳኑም ድንበር የተባለው ለትርጉም ስለሚያሻማ፣ መንግሥት ቃላት መረጣውን ሊያስብበት ይገባል። ድንበሩን ዘግቶ ለአሸባሪ ቀለብ መስፈሩ ሕጋዊ ስለማይሆን፣ ከክልሉ አካባቢዎች ሸሽተው ለሚመጡና እርዳታ ለሚፈልጉ በአጎራባች ክልሎች ጣቢያ ሊቋቋምላቸው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።
ክልሉ ውስጥ ያሉ እንደፈለጉ እንዳይወጡና እንዳይገቡ ከማድረግ ባለፈ፣ መንግሥት የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች እንፈልጋለን ብለው በሕጋዊ መስመር እስከሚመጡ ድረስ ማቆየት ያስፈልጋል። ቤትን ሊዘርፍ መጥቶ ሲነቃበት አንድ ክፍል ገብቶ አልወጣም ብሎ የቆለፈ ሰርሳሪ ሌባ፣ ሐሳቡን እስኪቀይር ተብሎ ምግብ እየበላህ ቆይ አይባልም። ግብረ አበሮቹም ደርሰው እንዳያስወጡት ይሉኝታ በሌለው መልኩ መግቢያና መውጫውን አጥሮ አማራጭ እስኪያጣ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል። ክፍሉ ውስጥ ሰው እያለ ከሆነ የቆለፈው የውስጥ ተባባሪው መሆን አለመሆነኑን ለማወቅ ከሌባው ጋር የነበረው ቆይታ ይወስነዋል።
ትግራይን መልሶ ተቆጣጠረ የተባለውን ቡድን ለአገር ስጋት መሆኑ ቀርቷል እያሉ በማቃለልና በመናቅ እንደደርግ ዘመን ስሕተት ላይ መውደቅ ተገቢ አይሆንም። ጠላት እኛን ንቆን በደንብ ሳይዘጋጅ እንዲመጣ ማድረግ እንጂ፣ ንቀነው እንድንዘናጋና ለደጋፊዎቹም መቀስቀሻ እንዳይሆነው መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ራስን የሚያኮስስ አገላለጸ የተባለው የሥነልቦና ጦርነት እንደመሆኑ ሕዝብ ላይ እንዲሁም የገዛ ጦርና የጠላት ታጣቂ ላይ የሚያሳድረው ጫና በግልጽ መታወቅ አለበት። ወጥነት በሌለው መልኩ በካድሬዎችና በደጋፊዎች እንዲሁም በባለሥልጣናት የሚደረጉ ንግግሮች ጊዜያዊ ጩኸትን ለማብረድ ሳይሆን፣ በይበልጥ የተቃራኒ ወገንን ድጋፍና ተቀባይነት ለመሸርሸር ያተኮሩ ሊሆኑ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ለትግራይ ክልል ከጦሩ ውጭ ለመሰረተ ልማት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጣ ተብሎ ከንፈር ተመጦ ዝም ማለት አይገባም። የክልሉ መሪ የነበሩ አካላት በፈጸሙት ተግባር ወጪ መደረጉ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ሕግ አሸባሪ የተባሉትን ሸሽጎ መልሶ ለዚህ ያበቃቸው አካል ለወደፊት ወጪውን እንዲሸፍን መደረግ አለበት።
በሌላ በኩል፣ ከእንግዲህ በክልሉ ለሚፈጸሙ ማናቸውም ተግባራት ተጠያቂው አሸባሪው ነው የሚሆነው የተባለው ምን ለማለት እንደሆነ ሊብራራ ይገባል። አልያዝ ያለን አካል ፍርድ ቤት አቁሞ ተጠያቂ ሁን ማለቱ የማይቻል ስለሆነ የበለጠ በራስ መተማመን እንዳይፈጥርላቸው ሊታሰብበት ይገባል። የኃይል ሚዛኑን በተመለከተ ሊወሩ የሚችሉበት አቅም እንደሌላቸው፣ መቐለም ከበሻሻ የምትሻልበት ሁኔታም እንደሌለ የተገለጸው ስጋት ያለበትን ሊያረጋጋ ቢችልም፣ እነሱና ደጋፊዎቻቸው አለን ለማለት ብለው በሚፈጽሙት ተግባር አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዳይከፈል ማሰብ ያስፈልጋል።
‹‹የመንግሥት ዓላማ መቀሌን ነፃ ማውጣት አይደለም›› የተባለው አገላለጽ ሕዝብን ግራ ያጋባ እንደሆነ ይነገራል። የተያዙብንን ለማስለቀቅ እንጂ ወረራ አይደለም ብሎ ማብራራት ያስፈለገው ለማን ነው? ሕዝቡ በሥሙ ምግብ እየተቀበለ እንደሚቀልባቸው እስከታወቀ ድረስ፣ ሉዓላዊ አገር እስካልሆኑ ድረስ ወረራ ሊባል እንደማይችል ግልጽ ነው። ጦሩ ሁሉን የሚያየው እንደጠላት ሁኗል እየተባለ፣ በሌላ ቦታ ያሉ ደጋፊዎቻቸው ላይ ድርጊታቸው ምን ሊፈጥር እንደሚችል ለራሱ ለሕዝቡ ማስተማር በተገባ ነበር። ደጀን ወደሆነ ሕዝብ መጠጋቱ አስፈላጊነቱ ባያጠራጥርም የሞት መሬቱን አካባቢ ለመቀየር መሞከሩ ተገቢ እንደሆነ ይታመናል።
ስምንት ወራትን የፈጀው ጦርነት በርካታ ውጊያዎችን አስተናግዶ እዚህ ቢደርስም፣ የተናጥል ተኩስ አቁም ሥምምነትም ይሁን እርምጃ አሸባሪ ከተባለ ጋር ማድረጉ የሠራዊቱን የመዋጋት ሞራል እንዳያላሽቀው የጊዜው ሁኔታ በደንብ ሊታሰብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። የጥሞና ጊዜው አስፈላጊ ቢሆንም፣ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ምስጢር ከመሆን ይልቅ፣ በወገኑ የታገተው ሕዝብ አውቆ እንዲታገለው ዕድል ሊሰጠው ይገባል። ትግራይ የቀሩ ተማሪዎችና ሠራተኞች በሠላም የሚመለሱበት መንገድም መታሰብ የነበረበት ቀድሞ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን የማስተካከያ ጊዜ ስላለ ያሉትን አማራጮች መፈተሸ ግድ ይላል። ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ፥ ባረም ይመለሱ›› እንደሚባለው፣ የተወሰደው የመፍትሄ እርምጃ ፍሬ የሚያፈራ እንዲሆን ጉልጓሎው ላይ ቢተኮር መልካም ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013



