“መንግሥት ካለ ችግራችንን ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሔ ይስጠን” ተፈናቃዮች
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥት እንዳልተቀበላቸው እና ምንም አይነት የሰብዓዊ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። በምሥራቅ ወለጋ በተደጋጋሚ በታጣቂ ኃይል በሚደርስ ጥቃት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከተፈናቀሉ አርሶ አደሮች መካከል ርቀው መሄድ ያልቻሉት በቅራቢያቸው ወደሚገኝ እና አንፃራዊ ሰላም ወደ አለበት አከባቢ ቢሸሹም ተቀብሎ ያስተናገዳቸው የመንግሥት አካል እንደሌለ ነው የገለጹት። ከጊዳ አያና ወረዳ አርቁንቢ መንደር አንድ፣ አርቁንቢ መንደር ኹለት፣ አርቁንቢ መንደር ሦስትና አርቁንቢ መንደር አራት የተፈናቀሉ ዜጎች በአሁኑ ጊዜ ከጥቃት ሸሽተው አንገር ጉትን ከተማ ላይ ይገኛሉ።
ይሁን እንጅ የተፈናቀሉ ዜጎችን እንደ ተፈናቃይ የሚቀበል እና መሠረታዊ የሚባሉ የመጠለያና ምግብ አቅርቦት ድጋፍ የሚያደርግ የመንግሥት አካል እስካሁን እንደሌለ ነው የተገለጸው። አንገር ጉትን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ እስካሁን በማኅበረሰቡ ትብብር በየበረንዳው ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል። አንገር ጉትን ከተማ ውስጥ የሚገኙ ከአራት ቀበሌዎች የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ከተፈናቀሉበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በማኅበረሰቡ መልካም ትብብር ቢቆዩም፣ አሁን ላይ የተፈናቀሉበት አካባቢ ከታጣቂዎች ነጻ ሆኖ ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው የእርሻ ሥራቸውን ማከናወን ይፈልጋሉ።
አርቁንቢ መንድር እንድ፣ አርቁንቢ መንደር ኹለት፣ አርቁንቢ መንደር ሦስትና አርቁንቢ መንደር አራት ይኖሩ የነበሩ አርሶ አደሮች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ቤት ንብረታቸውን ጥለው መውጣታቸወን ተከትሎ ተፈናቃዮቹ “ኦነግ ሸኔ” ያሏቸው ታጣቂዎች ሰሞኑን አካባቢዎቹን ተቆጣጥረዋል። በዚህም ባሳለፍነው ሳምንት በአርቁንቢ መንደር ኹለት ከሰባት በላይ የአርሶ አደሮች ቤቶች መቃጠላቸውን ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በተፈናቃይ አርሶ አደሮች ቤት የሚገኙ ንብረቶች ሰሞኑን አራቱን መንደሮች ተቆጣጥሯል በተባለው “ኦነግ ሸኔ” ተጭነው እንደተወሰዱም ተፈናቃዮች ጠቁመዋል።
ተፈናቃዮች አሁን የሚገኙበት አንጻራዊ ሰላም አለው የተባለው አካባቢ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በአካባቢው ተሰማርቶ ነበር ተብሏል። ይሁን እንጅ ከሳምንት በፊት የአካባቢውን ጸጥታ የሚያስከብረው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ይህንን ተከትሎ አርሶ አደሮችን አፈናቅሎ በቦታቸው ላይ እየተንቀሳቀሰ ነው የተባለው የታጠቀው ኃይል፣ ወደሚገኙበት አካባቢ ገብቶ ጥቃት እንዳይፈጽም ስጋት እንዳላቸው ተፈናቃዮች ተናግረዋል። ስጋታቸውን የገለጹት ተፈናቃዮች “መንግሥት ካለ ችግራችንን ተመልክቶ አፋጣኝ መፍትሔ ይስጠን” ሲሉ ጥሪ አቅረበዋል። አክለውም መንግሥት አካባቢው ላይ ያለውን ስጋት ተመልክቶ ሕዝብ ከመጎዳቱ በፊት ቦታውን እንዲፈትሸ ጠይቀዋል።
አርሶ አደሩ የእርሻ መሬቱን ትቶ በመውጣቱ በተያዘው የምርት ዘመን ማረስ አልተቻለም። ይህ ደግሞ አርሶ አደሩ አሁን ላይ የሰብዓዊ ድጋፍ ማግኘት ባልቻለበት ሁኔታ ላይ ሆኖ ሳለ፣ ለወደፊቱም የችግር ሰለባ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013



