ወደ ሥራ የገቡ አዲስ የምግብ ዘይት አምራቾች በኃይል አቅርቦት እየተቸገሩ መሆኑን ገለጹ

0
1382

በቅርብ ጊዜ ግንባታቸውን ጨርሰው ወደ ምርት የገቡ የምግብ ዘይት አምራቾች በኃይል አቅርቦች ችግር ምክንያት ማምረት በሚችሉት አቅም እያመረቱ እንዳልሆነ ገለጹ። ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ምርት ሥራ የገቡ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው አንዳንዶቹ ሙሉ ሰዓት በጀነሬተር እያመረቱ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሚያመርቱበት ሰዓት ግማሽ ያክሉን በጀነሬተር እየተጠቀሙ እንደሆነ ገልጸዋል። በቅርቡ አዲስ የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ አስገንብተው ወደ ሥራ የገቡት በላይነህ ክንዴ፣ ፋብሪካቸው ከሚጠቀመው የማምረቻ ሰዓት ውስጥ ግማሽ ያክሉን የሚያመርተው በጀነሬተር ኃይል መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰኔ 21/2013 በምግብ ዘይት አምራቾች ችግር ላይ ትኩረቱን ባደረገ ውይይት ላይ ተገኝተው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በቡሬ ከተማ የተገነባው ንብረትነቱ የበላይነህ ክንዴ የሆነው ፊቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያን የዘይት ፍላጎት 60 በመቶ የሚሸፍን እንደሚሆን ተነግሮለታል። ፋብሪካው ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ በቀን 1500 ቶን ያህል የምግብ ዘይት ማጣራት እና መሙላት የሚችል ነው ተብሏል። ይሁን እንጂ ፊቤላ ዘይት ፋብሪካ ግማሽ የምርት ሰዓቱን የሚጠቀመው በጀነሬተር መሆኑን ነው ባለንብረቱ የገለጹት። እንደ በላይነህ ገለጻ ከሆነ ትልልቅ የሚባሉ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፉን ቢቀላቀሉም፣ በሙሉ አቅማቸው ለማምረት በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው አብራርተዋል። ከችግሮቹ መካከል የኃይል አቅርቦት እጥረት አንዱ ሲሆን፣ ለምግብ ዘይት ምርት እንደ ጥሬ ዕቃ የሚያገለግሉት የቅባት ዕህሎች ምርት መቀነስም ከቀዳሚ ችግሮች መካከል የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

የምግብ ዘይት አምራቾች ችግር ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተካሄደው ውይይት ላይ ጤና ዘይትን ወክለው የተገኙት አብርሃም መኮንን፣ በቅርቡ “አርት ክራፍት ኢንዱስትሪ” የተባለ አዲስ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ሥራ ቢገባም እስካሁን ድረስ የኃይል አቅርቦት እንዳላገኘ ጠቁመዋል። በመሆኑም ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ምርቱን የጀነሬተር ኃይል ተጠቅሞ እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል። ፋብሪካው የሚጠበቅበትን ቅድመ ሥራ አጠናቆ ቆጣሪ አስገብቶ የኃይል አቅርቦት ማግኘት እንዳልቻለ ነው የተናገሩት።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከምግብ ዘይት አምራቾች ጋር ባደረገው ውይይት ወቅት የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ዋና ዋና ችግሮችን ለመፍታት የቀረበ ጥናት እንደሚስረዳው ከሆነ፣ የቀጣይ ኹለት ዓመታት የዘይት ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት፣ በ2014 የሰባት በመቶ የሚሆን ሲሆን፣ በ2015 የዘጠኝ በመቶ የአቅርቦት ክፍተት ይኖራል ተብሏል። የ2014 የምግብ ዘይት ፍላጎት በወር 75 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር ሲሆን፣ በዓመት 906 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር ነው።

በጥናቱ ላይ የቀረበው ሌላኛው ችግር የቅባት እህል ምርት እጥረት ሲሆን፣ ከ2007 – 2012 ባሉት ዓመታት አጠቃላይ በአገር ውስጥ የእህል ምርት ለማምረት ከለማው መሬት የቅባት እህል ለማልማት የዋለው የእርሻ መሬት የሚሽፈነው በአማካይ 6 ከመቶ ብቻ ነው።
በዚህ የእርሻ መሬት ላይ የሚመረተው የቅባት እህል በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚመረተው የእህል ምርት በአማካይ 2.7 ከመቶ ብቻ የሚሸፍን ነው። በመሆኑም የምግብ ዘይት አምራቾች ከፍተኛ የቅባት እህል አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እንገደጠማቸው ተገልጿል። ይህንኑ ተከትሎ አምራቾች በምርታቸው ላይ ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉ እንዳስገደዳቸው ጠቁመዋል።

የዘይት አምራች ፋብሪካዎች ዓመታዊ የማምረት አቅም ከ89 ሚሊዮን ሊትር ቶን ወደ 1.25 ቢሊዮን ሊትር ማደግ መቻሉ የተጠቆመ ሲሆን፣ በዘርፉ የተገኘው ስኬት አገራዊ የዘይት ፍላጎትን በራስ አቅም ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ ነው ተብሏል። የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ቢያድግም፣ በገጠሟቸው ችግሮች ማምረት የሚችሉት ከአቅማቸው ከግማሽ በታች ነው። አጠቃላይ የዘይት ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት ከ 5 በመቶ ወደ 40 በመቶ ማሳደግ መቻሉ የተገለፀ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሁኔታ 60 በመቶ የዘይት የምግብ አቅርቦቷን የምታሟላው ከውጭ በማስገባት ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here