ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በስብሰባውም እየተገባደደ ባለው 2013 በጀት ዓመት የተደቀኑ ፈተናዎችን በመቋቋም የተሻለ አገራዊ እድገት እንደሚመዘገብ የገለፁት ጠቅላይ ሚንስትሩ የኮቪድ ወረርሽኝ ጫና እና የአንበጣ መንጋ በግብርና ምርታማነት ላይ ያደረው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደነበር ገልፀው የአንበጣ መንጋው እርሀብን ባያስከትልም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ለቀሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚወጣው ወጪ፣ የጎርፍ መከሰት እና በፖለቲካው አለመረጋጋት ምክንያት የተከሰቱ የዜጎች መፈናቀሎች ለዋጋ ንረቱን ማባባሳቸውንም አነስተዋል፡፡
እንደ ማዳበሪያ እና ነዳጅ ባሉ ምርቶች አቅርቦት ላይ ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት ማነቆ ሆኖ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በ2013 የሀገሪቱ እድገት ተሰርቶ ይፋ የሚሆነው በቀጣይ መስከረም ወር ቢሆንም እስካሁን ግን በመኸር እና በልግ ወቅት ጥሩ አፈጻጸም እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ባልተለመደ ሁኔታ የበጋ ስንዴ ተሞክሮ ከ15 ሚሊየን በላይ ኩንታል መመረቱን አንስተው ዘንድሮ በግብርናው ዘርፍ በተፈጠሩ አመቺ ሁኔታዎች እና በወጪ ምርት አፈፃፀም ላይ በታየው መሻሻል ምክንያት አምና ከተመዘገበው 6 በመቶ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በማዕድን ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ መገኘቱን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚንስትሩ የሀገሪቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት በውጭ ከ100 ቢሊዮን በሀገር ውስጥ 4.2 ትሪሊዮን በላይ መድረሱን አንስተዋል።
የኢንቨስትመንት ዘርፉም ሀያ በመቶ እድገት ማሳየቱንና ይህም የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር እና የቁጠባ ባህል እያደገ መምጣት በቀጣይ ላለው የኢኮኖሚ እድገት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስተሩ አክለውም በባንክ የሚዘዋወር ብር ከ1 ትሪሊዮን በላይ መሆኑን ገልፀው በገቢ እና ውጭ ሚዛን ላይ ያለው ልዩነት 9.3 መድረሱንም ገልፀዋል።
በተቸማሪም የእዳ ጫናን ለመቀነስ በተሰራው ስራ ጫናው እየቀነሰ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለመበደር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልፀው በቀጣይ ሁለት ዓመታት ደግሞ ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት ጥረቶች እንደሚደረጉም አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም በዚህ አመት ኢትዮጵያ 3.5 ቢሊዮን አካባበቢ ከውጭ ገበያ ማግኘቷን ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ የውጭ እዳ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት 37 በመቶ ነበርና በአሁኑ ሰዐት ወደ 26 በመቶ መውረዱንም በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ገልፀዋል።



