የሰኔ ወር ዋጋ ግሽበት 24 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳየ

0
863

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በየወሩ የሚያወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ ሁኔታ መሰረት የሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ24 ነጥብ 5 ከመቶ ጭማሬ ማሳየቱ ተገለፀ፡፡

በመረጃው መሰረትም የምግብ ዋጋ ግሽበት የሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ28 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በዳቦና እህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በያዝነው ወርም የቀጠለ ሲሆን በተለይ የበቆሎና የገብስ ዋጋ በፍጥነት ጨምሯል፡፡

በተጨማሪም ሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም፣ በርበሬና ቡና የዋጋ ጭማሪ በዚህም ወር በመቀጠላቸው ለዋጋ ግሽበት ምጣኔ በፍጥነት መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል።

ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ከአሁኑ ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በንጽጽር ዝቅተኛ ስለነበር የዋጋ ግሽበቱ በያዝነው ወርም ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ19 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ታውቋል፡፡

ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮል፣ ልብስና ጫማ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መስሪያ እቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶና የቤት ኪዳን ቆርቆሮ)፣ ህክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡

አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር ሰባት ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ ለኢፕድ በላከው መረጃ አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here