በአማራ ክልል 20 ወረዳዎች ላይ የወባ ወረርሽኝ መከሰቱን የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጸው፣ በሽታው በስፋት ይከሰትባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ወራቶች ቀድሞ መስፋፋት ጀምሯል። በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ አብርሀም አምሳሉ፣ አሁን ላይ በክልሉ 20 ወረዳዎች ላይ በወረርሽኙ ሰዎች እየታመሙ ነው ብለዋል። ወረርሽኙ የታየባቸው በስፋት በምዕራብ አማራ ያሉ እንደ ምዕራብ ጎንደር ፣ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች መሆናቸውን አንስተዋል።
ቦታዎቹም ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ሰፋፊ የልማትና ውኃማ ቦታዎች የሚገኙባቸው፣ ከልማት ኮሪደር ጋር ተያይዞ የሰዎች እንቅስቃሴ የሚበዛባቸው መሆን አሁን ላይ ለበሽታው መስፋፋት እንደ ምክንያት ከቀረቡት ተጠቃሾቹ ናቸው። በሽታው በወረርሽኝ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው መተማ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። በክልሉ ያለውን ወረርሽኝ ለመቀነስ የቀረቡ ግብዓቶችን የማሰራጨት ሥራዎችም እየተሠሩ መሆኑን አመላክተዋል። በ 59 ወረዳዎችም 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን አጎበር እየተሰራጨ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የኬሚካል ርጭት ሥራም መሠራት መጀመሩን ገልጸዋል።
45 ያህል ወረዳዎችም ቀድሞ የኬሚካል ርጭት እንደተከናወነባቸው ነው አቶ አብርሀም የተናገሩት። በክልሉ ወረርሽኙ በስፋት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ በጤና በለሙያዎች የቤት ለቤት የምርመራና የህክምና ሥራዎች የማከናዎን ተግባር ተጀምሯል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። ወረርሽኙን ለመቀነስ በተቋም ደረጃ ከሚሠሩ የመከላከል ሥራዎች በተጨማሪ፣ የተሰራጩ አጎበሮችን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም ለወባ ትንኝ መራቢያ የሚሆኑ ቦታዎችን ማስወገድ እና መሰል ጥንቃቄዎችን ማድረግ ከሕብረተሰቡ የሚጠበቅ ግድታ እንደሆነም አንስተዋል። የወባ በሽታ ህክምና በመንግስት ተቋማት በነጻ እየተሰጠ መሆኑን ያሳወቀው ኢንስቲትዩቱ፣ የበሽታው ምልክት የሚታይበት ኹሉ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እንዲታከም አሳስቧል።
ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013


