በአዲስ አበባ የወሲብ ንግድ አስፋፍተዋል የተባሉ ማሳጅ ቤቶች ሊታሸጉ ነው

0
1544

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ለማሳጅ አገልግሎት ተብለው የተከፈቱ ቤቶች የወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ተብሏል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በከተማዋ በርካታ የማሳጅ ቤቶች ከሕግ ውጭ የሆነ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን አስታውቋል። የፖሊስ ኮሚሽኑ የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ እንደተናገሩት በማሳጅ ስም የወሲብ ንግድ የሚሠሩ ቤቶች እየተበራከቱ ነው። እንደ ኮማንደር ፋሲካ ከሆነ ሊገመቱ የማይችሉ ቤቶችም በዚህ ሥራ ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።
ፖሊስ ኮሚሽኑ በከተማዋ በበርካታ አካባቢዎች ጥቆማ እየደረሰው መሆኑን ጠቅሶ፣ የመለየት ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው። አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ ሰፈሮች ቦሌ መንገድ ውስጥ ለውስጥ አትላስ አካባቢ ቺቺኒያ ተብሎ የሚጠራው፣እንደዚሁም 22 አካባቢ ችግሩ በብዛት የሚስተዋልባቸው ናቸው ተብሏል። ማሳጅ ቤት ተብለው የተከፈቱት ቤቶች አብዛኛዎቹ ቀን ላይ ሥራ እንደማይሠሩ እና ምሽት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም አንዳንዶቹ ማሳጅ ቤቶች የሱስ ማዘውተሪያ የሆኑበት አጋጣሚም እንዳለ ነው ኮማንደር ፋሲካ የገለጹት። በእነዚህ ቤቶች ላይ የተጀመረው የማጣራት ሥራ ሲያልቅ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ኮሚሽኑ አስታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here