ወደ ትግራይ በሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግ የበረራ ዝግጅትን በተመለከተ የፌደራል መንግስት ያወጣው መግለጫ

0
721

የፌደራል መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግ የበረራ ዝግጅትን በተመለከተ በዛሬው እለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መግለጫ አውጥቷል። የመግለጫውም ሙሉ ሀሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል

የኢትዮጵያ መንግስት ሁለገብ የተኩስ አቁም አዋጅ ማወጁ ተከትሎ በሰብአዊ አገልግሎት ከሚሰማሩ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ በተደጋጋሚ አረጋግጧል፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከግንቦት 13/2013 ዓ.ም ጀምሮ ከበረራ ደረጃ 290 በታች ለሆኑ ሁሉም በረራዎች የሰሜኑን የአየር ክልል ዘግቶ የነበረ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል የሰብአዊ አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው ወገኖች  እንዲበሩ ልዩ ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስት ሸቀጣ ሸቀጦችን እና ተሳፋሪዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለማመላለስ የሚቀርብን ማንኛውንም ጥያቄ እንዳልከለከለ ለማሳወቅ ይፈልጋል፡፡

በእርግጥ የአለም የምግብ ፕሮግራም ትናንት ተሳፋሪዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለማብረር ለሚፈልጉ ሁለት አውሮፕላኖች የበረራ ፍቃድን ጠይቋል፡፡

እነዚህን የመሰሉ ጥያቄዎችን በተሻለ ሁኔታ ለማመቻቸት የፌዴራል መንግስት የሰብአዊ አገልግሎት ሰጭዎች፣ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሚመለከታቸው አካላት ፈቃድ ለማግኘት በጥብቅ መከተል ያለባቸውን መመሪያዎችንና መረጃዎችን የያዘ መመሪያ አውጥቷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት ከውጭ ወይም ከአገር ውስጥ አየር ማረፊያዎች ለሚመጡ በረራዎች ሁሉ ወደ ትግራይ ከመሄዳቸው በፊት በመጀመሪያ አዲስ አበባ አየር ማረፊያ ማረፍ እንዳለባቸው በግልፅ አስቀምጧል፡፡

ከተከለከለው የአየር ክልል የሚመጡ በረራዎችም ወደ ውጭ ከመሄዳቸው በፊትም ሆነ በአገር ውስጥ አየር ማረፊያዎች ከመጓዛቸው በፊት በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ማረፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በመመሪያዎቹ ውስጥ በዝርዝር እንደተመለከተው ሁሉም ኦፕሬተሮች የበረራ ዝርዝሮችን ማለትም የአውሮፕላን ዓይነት፣ የበረራው ዓላማ፣ የተሳፋሪዎች ዝርዝር እና የጭነት ዓይነትን በረራ ከማከናወናቸው በፊት ማቅረብ እና ማረጋገጫ ማግኘት አለባቸው፡፡

ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚነሱ እና በሚያርፉ አውሮፕላኖች፣ በካርጎዎች፣ በተሳፋሪዎች፣ በሠራተኞች ላይ እንዲሁም ለምርመራ እና ለማጣራት መበታተን የሚያስፈልጋቸውን ግዙፍ ካርጎዎችን ጨምሮ መደበኛና ደረጃውን የጠበቀ ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጻል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ሁሉም የመንገደኞች እና የጭነት አውሮፕላን በረራዎች ከሰብዓዊ ዕርዳታ ተልዕኮዎች ጋር ብቻ የሚዛመዱ ሰዎችን ወይም መሣሪያዎችን እንዲጭኑ ይጠይቃል፡፡

ከላይ የተገለጹት ዝግጅቶችን እና የፌዴራል መንግስት ከሰብአዊ አገልግሎት ሰጭ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ፈቃደኛ ቢሆንም፤ አንዳንድ ዘገባዎች በስህተትም ይሁን በሌላ መንገድ መንግስት ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎችን የሚያደናቅፍ በማስመሰል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ መረጃ መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት እያከናወነ ያለው የማይገባ ድርጊት ሀገሪቱ ከድርጅቱ ጋር ካላት ፍሬያማ ግንኙነትን የማይመጣጠን በመሆኑ ይህንንም በመቃወም ለተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ ደብዳቤ ጽፏል ፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ 1984 ጀምሮ ከድርጅቱ ጋር ጠንካራ የሚባል ግንኙነትን ገንብታለች፡፡

የፌዴራል መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በትግራይ ያለውን ሁኔታ በሚገልፁ ትክክለኛ ባልሆኑ ሪፖርቶች እና መግለጫዎች በትግራይ ክልል ውስጥ የህግ ማስከበር ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እያወጣ በመሆኑ ይህም ሀገሪቷ ከድርጅቱ ጋር ላላት ጠንካራ ግንኙነት ጠቃሚ እና ገንቢ እንዳልሆነ ያምናል ፡

የፌዴራሉ መንግስትም የጽህፈት ቤቱ መግለጫዎች እና ሪፖርቶች የተሳሳተ አስተሳሰብን እያጠናከረ የቀጠለውን ህወሃትን ለማበረታታት እና ለማወደስ ​​የተቀየሰ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በክልሉ ያለውን ሁኔታ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳ የሚያደርግ ይመስላል፡፡

ጽህፈት ቤቱ የኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት የፈረጀውን ህገ-ወጥ ቡድንን የትግራይ መከላከያ ሰራዊት (TDF) እያለ መጠቀሙንም እንደቀጠለ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለጽህፈት ቤቱ አድሎአዊና አሳሳች መግለጫዎችን ከመስጠት እንዲቆጠብ እና በኢትዮጵያ መንግስት እና በድርጅቱ መካከል ለረጅም ጊዜ በሚሰራው ትብብር ላይ ጎጂ ውጤቶች እንዳይከሰቱ በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስድ ይጠይቃል ፡፡

ወደ ትግራይ ክልል የበረራ ዝግጅቶች ዝርዝር መመሪያዎች በቅርቡ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ፍላጎት ላላቸው አካላት እንዲሁም ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ እንደሚተላለፉ የኢፌዴሪ መንግስት ለመግለጽ ይፈልጋል ፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here