የአማራ ክልል መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው የህወሓት ቡድን በተከፈተበት ይፋዊ ጦርነት ራሱን ከመከላከል ወጥቶ ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር መወሰኑን አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸም የአማራ ክልል በህወሓት አሸባሪ ቡድን በዋግ ግንባር አበር ገሌ፣ ፀጋብዲና በዛታ፤ በራያ ግንባር በኮረም፣ አለማጣ እና ባላ፤ በወልቃይት ግንባር በማይፀብሪ እና በጠገዴ ለተከፈተበት ይፋዊ ጦርነት ራሱን ከመከላከል ወጥቶ ወደ ማጥቃት እንደሚሸጋገር አስታውቀዋል።
ክልሉ በሦስቱ ግንባሮች የተከፈተበት ጦርነት ዓለም አቀፋዊ የጦርነት ህጎችን በሚፃረር መልኩ ህፃናት፣ አረጋውያንን፣ የኃይማኖት አባቶች እና ሴቶችን ከፊት በማሰለፍ ንፁኃንን በመተንኮስ እና በመግደል የታጀበ ይፋዊ ጦርነት መሆኑንም ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ ክልሉ ወራሪውን ኃይል ለመከላከል እና ለመመከት ብቻ ሲጥር እንደቆየ በመግለፅ፣ ከዚህ በኋላ ግን የክልሉ ልዩ ኃይል እና አጠቃላይ የፀጥታ አካላት ወደ ማጥቃት እንዲሸጋገሩ ትእዛዝ መሰጠቱን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የገለፁት።
በክልሉ በኩል ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር የሎጂስቲክስ ችግር አለመኖሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ በተለይም በትጥቅ እና በሰው ኃይል በኩል ምንም አይነት ክፍተት አለመኖሩን ጠቁመዋል።
ሆኖም ግን ከህብረተሰቡ የሚደረገው ሁለገብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለይም ወጣቱ በልዩ ኃይል እና በሚሊሻ እንዲደራጅ፣ ምልስ የሠራዊት አባላትም በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ምላሽ እንዲሰጡ ኃላፊው ማሳሰባቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም እና የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮችን ጨምሮ በርካታ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የአንድ ወር ሙሉ ደሞዛቸውን መለገሳቸውን በማስታወስ ፣መላው ህብረተሰብም ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ ሁለገብ ድጋፉን ለክልሉ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።



