የ4ዓመት ከ9ወር ዕድሜ ያላትን ህጻን ከትምህርት ቤት አግቶ በመውሰድ ገንዘብ የጠየቀው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

0
955

 

የ4ዓመት ከ9ወር ዕድሜ ያላትን ህጻን ከትምህርት ቤት አግቶ በመውሰድ ገንዘብ የጠየቀው ግለሰብ በተደረገበት ብርቱ ክትትል ከአዲስ አበባ ውጪ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የእገታ ወንጀሉ የተፈፀመው ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 10 ሰዓት ተኩል ገደማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደገለፀው ተጠርጣሪው ግለሰብ የህፃኗ ወላጆች ንብረት በሆነ ሆቴል ውስጥ ለ2 ዓመታት ያህል በጥበቃ ሰራተኝነት እያገለገለ የቆየ ሲሆን በዕለቱም ህፃኗን ከምትማርበት ት/ቤት እንዲያመጣት በወላጆቿ ሲታዘዝ እሱ ግን የታዘዘውን ወደ ጎን በመተው ህፃኗን ይዞ መሰወሩን እና ልጃችሁን አግቻታለሁ 250 ሺህ ብር አዘጋጁ ካለበለዚያ አታገኟትም የሚል ማስፈራሪያ በስልክ ሲያደርሳቸው ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የክትትልና ኦፕሬሽን ክፍል የህፃኗ መጥፋት ሪፖርት ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ ተጠርጣሪውን የማፈላለግ ስራ ሲሰራ ቆይቶ በታገተች በሁለተኛው ቀን ሃምሌ 01 ቀን 2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ ውስጥ ህፃኗን ይዞ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ እየተጣራ መሆኑንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም ሚያዚያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ20 ገደማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ሰለሞን ምንዳ ጠጅ ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የግል ተበዳይ የወ/ሮ መዓዛ ገረመው ልጅ የሆነ የ15 ዓመት ህፃን እያዩ መሰረት በሚባል እና በግል ተበዳዮች ቤት ተቀጥሮ በሚሰራ ግለሰብ ታግቶ እንደተወሰደ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውሷል፡፡

ግለሰቡ ህፃኑን በመውሰድ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም አባይ ማዶ ወይንዬ በረሃ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በማስቀመጥ እና የህፃኑን ወላጆች ገንዘብ እንዲያመጡ በማስገደድ ካላመጡ ግን እንደሚገድለው ይዝት እና ያስፈራራ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የምርመራ እና የክትትል ቡድን በመቀናጀት ባከናወኑት ተግባር ተጠርጣሪውን በ6 ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር አውለው ህጻኑን በመልካም ጤንነት ይዘው መመለሳቸውን ከወንጀል ምርመራ ክፍሉ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

በተከሳሽ እያዩ መሰረት ላይ የምርመራ መዝገብ በማደራጀት ክስ እንዲመሰረት ከተደረገ በኋላ ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የተከሳሹን ጥፋተኝነት በማረጋገጥ በ7 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ያስተላለፈበት መሆኑ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here