የብሄራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂን በይፉ የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተከናወነ
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የአገሪቱ አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን የክፍያ ዘዴዎችን ለማዘመንና እንደ አገር በ2025 እ.አ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተቀመጠውን እቅድ እውን ለማድረግ የሚያስችል የሶስት አመት የብሄራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ማስጀመሪያ መርሀ ግብርን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን አስጀምሯል።
በመድረኩም የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢዎች፣ የባንክ ስራ አመራር አባላት የተባበሩት መንግስታት የልማት የካፒታል ፈንድ አመራሮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የብሄራዊ ዲጂታል ክፍያ መርሀ ግብሩ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተወዳዳሪ፣ ወጪ ቆጣቢና ሀላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ የክፍያ ከባቢያዊ ሁኔታ በመገንባት ውስን ጥሬ ገንዘብን የሚጠቀምና የፋይናንስ አካታችነትን የተላበሰ ኢኮኖሚ እንዲኖር የማገዝ አላማን መያዙን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የክፍያ ሥርዓትና ሴትልመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ማርታ ሀይለማርያም አስረድተዋል።
ዳይሬክተሯ አክለውም የዲጅታል የክፍያ አገልግሎት ሥርዓት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግስት ባሉ የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማት ውስጥ የሚጫወተው ሚና ጉልህ እንደሆነ ገልፀው ይሄንንም ሥርዓት ወደ አገር ውስጥ በማስገባ ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንን የብሄራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስና ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርገው የተባበሩት መንግስታ ካፓታል ዲቨሎፕመንት በአፍሪካ ሃላፊ የሆኑት ኦስዌል ካኦንዴ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት አለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት እየሆነ እንደመምጣቱ ሥርዓቱን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የክፍያ መረጃው ተጠብቆ በእኩል የሚስተናገድበትና የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዎል።
የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ሰፊ፣ ውስብስብ እና ባለ ብዙ አውድ አጀንዳ በመሆኑ ዲጂታል ክፍያን ለማሳደግ በተለያዩ ሴክተሮች እና የኢኮኖሚ አውታሮች የሚገኙ ባለ ድርሻ አካላትን ተሳትፎና የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅም በመድረኩ ተገልጿል።
በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ ከተገኙ የባንክ አመራሮች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ለተነሱ ጥየቄዎችና ሀሳቦች ከመድረኩ መልስ ተሰጥቶባቸዎል።



