በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ላይ ለማቀርባቸው ምስክሮች ጥበቃ ይደረግላቸው ሲል ዐቃቤ ህግ የጠየቀውን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉ ተገለፀ።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዛሬ ባስቻለው ችሎት ላይ ነው ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ የተገለፀው፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ከአንድ እስከ አራት ያሉት ተከሳሾች ጠበቃ አቶ ቤተ-ማርያም አለማየሁ ዐቃቤ ህግ ለምስክሮቹ ሦስተኛ ወገን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ፍርድ ቤቱን መጠየቁን ለአሻም ቲቪ አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹ ከመጋረጃ ጀርባ ምስክርነታቸውን ይሰጡ ብሎ ቢጠይቅም በተመሳሳይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማደረጉን ጠበቃው አስታውሰዋል፡፡
ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ዐቃቤ ህግ ለሐምሌ 8፣ 9፣ 14፣ 15 እና 16 ቀን 2013 ዓ.ም. 21 ምስክሮች ቃላቸውን እንዲሠጡ ቀጠሮ አስይዞ ነበር፡፡
ይሁንና ዐቃቤ ህግ ዛሬ ባስቻለው ችሎት ለምስክሮቹ ጥበቃ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ በጀት ያስፈልጋል የሚል መከራከሪያ ሀሳብ ማንሳቱ ተገልጿል፡፡
የተከሳሾች ጠበቃ እንዳሉት ፍርድ ቤቱ ይህን መከራከሪያ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
በዚህም ከሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን እንዲያሰማ ማዘዙን አቶ ቤተ-ማርያም አረጋግጠዋል ሲል የዘገበው አሻም ነው፡፡



