የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የሞባይል መመርመሪያ መሳሪያውን (celebrate Machine) በ110,600 ዶላር ወጪ ከእስራኤል ሀገር በመግዛት ወደስራ ለማስገባት ለሙያተኞች ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ በስልጠናዉ ላይ በመገኘት በሰጡት የስራ መመሪያ መሳሪያው የስራ ዘርፉን ይበልጥ ለማደራጀት በርካታ ገንዘብ ወጪ ተደርጎበት የተገዛ በመሆኑ ባለሙያዎቹ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያዉሉ አሳስበዋል፡፡
የሳይበር ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዥን ሀላፊ የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር ዳኜ ነጋሽ ማሽኑን በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት መሳሪያዉ ዘመናዊነትን የተላበሰና አሁን አለም በዘመናዊ መንገድ የሚጠቀመዉ ስለሆነ ማናኛዉንም ሞባይል መመርመር የሚያስችል ነዉ ብለዋል፡፡
በቀጣይም የወንጀል ምርመራ ቢሮዉ የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የተለያዩ ዘመናዊ የሆኑ የመመርመሪያ መሳሪያዎችን ወደስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል ሲል የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታውቋል፡፡





