በመድሀኒትና በህክምና መሳሪያዎች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የሚመለከተው አካል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ተባለ

0
791

በመድሀኒትና በህክምና መሳሪያዎች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የሚመለከተው አካል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ።

በመድሀኒት እና በህክምና መሳሪያዎች ዙሪያ የተወሳሰቡ ችግሮች በመኖራቸውና በጤናው ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከዘርፉ ውጪ ማሰብ ስለማይቻል የአማካሪዎች ኮሚቴው ጠንካራ የመፍትሔ ሃሳቦችን ያመነጫል የሚል ዕምነት እንዳለው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በመድሀኒት እና በህክምና መሣሪያዎች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ታልሞ የተቋቋመው የአማካሪዎች ኮሚቴ በተዘጋጀው የመነሻ ሀሳብ ላይ የመጀመሪያ ውይይቱን ባካሄደበት መድረክ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒሰቴር ሚኒሰትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በመድሀኒትና በህክምና መሣሪያዎች ማምረት፣ መሸጥ፣ መግዛትና መጠቀም ዙሪያ ያሉ የተወሳሰቡ ችግሮችን ለመፍታትና የተሻሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያስችሉ የውሳኔ ምክረ ሀሳቦችን ኮሚቴው ያቀርባል የሚል ዕምነት አለኝ ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ያዕቆብ ሰማን በበኩላቸው የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎችን የማምረቱ ጉዳይ በቀጣይም በመንግስት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሰራባቸው ቀዳሚ መሆኑን ገልፀው አማካሪ ኮሚቴው ችግሮችን ከመዘርዘር ባለፈ ጠንካራና ለውሳኔ የሚረዱ የመፍትሄ ሀሳቦችን ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

በመድሀኒት እና በህክምና መሳሪያዎች አጠቃቀም ፣ አመራረት ፣ግዢና ሽያጭ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ለመድረኩ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት በጤና ሚኒስቴር የመድሃኒትና ህክምና መሳሪያዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረጋሳ ባይሳ ችግሮችን ለመቀነስ በሚያስችሉ የውሳኔ ሀሳቦች ዙሪያ ፈጥነን በመምከር የዘርፉን ማነቆዎች ማቃለል ይጠበቅብናል ብለዋል።

ዘርፉ የሚመራበትን የቆየ ፖሊሲ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር አስተሳስሮ መከለስ እንደሚገባ ያሳሰቡት የኮሚቴው አባላት የተወጣጡት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከፋርማሲ ማህበር ፣ከመድሀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ፣ ከላብራቶሪ ባለሙያዎች ማህበር፣ ከመድሀኒት አምራች ፋብሪካዎች ማህበር፣ ከክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ ከመድሀኒት አስመጪዎች ማህበር እና ከጤና ሚኒስቴር መሆኑ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካገኘነው መረጃ ማወቅ ተችሏል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here