ሴቶች ጦርነትና ችግር ሲኖር ቅድሚያ የችግሩ ተገላጭ በመሆናቸው ለመከላከያ ሠራዊቱ በኹሉም መልኩ ድጋፎችን በመስጠትና አካባቢያቸውን ሠላም በመጠበቅ ረገድ ለሠራዊቱ ያላቸው ድጋፍ ማሳየት አለባቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ።
በአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ከአዲስ አአባ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት በጋራ አዘጋጅነት ”ክብር ለመከላከያ ሠራዊት” በሚል ከከተማዋ የሴት አደረጃጀቶችና ሲቪክ ማኅበራት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸው ታውቋል።
በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዛሬው መድረክ ዋና አላማ በትግራይ ክልል በሚካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተግባር ላይ ብዥታ እንዳይፈጠር ለማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተሳሳተ የፖለቲካ ስብከት የትግራይ ህዝብ የተነገረውን ሀሰተኛ መረጃ በመከላከያ ሠራዊቱ ጥንቃቄና በመንግሥት ከፍተኛ ውሳኔ ህዝቡ ቆም ብሎ እንዲያይና የጽሞና ጊዜ እንዲኖረው መደረጉን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኑ መልሶ የአጥፍቶ መጥፍት ተግባር ህጻናትን በማሰለፍ እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
ድርጊቱም በኢትዮጵያ አንድነትና አብሮነት ላይ ያነጣጠረ እንጂ አንድ አካባቢን ብቻ የማጥቃት ጉዳይ አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።
ሴቶች ጦርነትና ችግር ሲኖር የጉዳቱ ቅድሚያ ተጎጂዎች እንደመሆናቸው ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም በሞራል በአቅርቦትና በሌሎችም ልዮ ልዮ መንገዶች ድጋፍ መስጠት አለባቸው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሴቶች የአካባቢያቸውን ሠላም በመጠበቅ ረገድም ለሠራዊቱ ያለንን ድጋፍ ማሳየት አለብን ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ በየአካባቢው ያለውን ተጋላጭ ሁኔታ በመጠበቅ የከተማዋን ሠላም መጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ይህንንም ስናደርግ የልማት ሥራዎቻችንን ጎን ለጎን በመሥራት ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ሴቶች በአገራዊ ጉዳይ እንዲሳተፉና ለመከላከያ ሠራዊቱ ያላቸውን ድጋፍ እንዲያሳዩ መደረጉ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሴቶች ስንቅ ከማቀበል ጀምሮ የአብሮነት ድጋፍ በመስጠት ከሠራዊቱ ጎን መሆናችንን እናሳያለን ማለታቸውም ታውቋል።





