አገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በጋራ ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌለ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ማህመድ ገለጹ፡፡
የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለማምከን በሚደረገው እንቅስቃሴ የሱማሌ ክልል የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት የጸጥታ ኃይል ወደ ቦታው ለማስመራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እንደገለጹት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት በአገር መከላከያ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው የህግ የማስከበር ዘመቻ የተለያዩ ምዕራፎችን አልፏል፡፡ በዚህ ሂደት የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚሰጣቸው ምክንያቶች ይለዋወጡ፣ ሀሳቦቹ ይቀያየሩ እንጂ የሚከተለው አገር የማፍረስ አጀንዳ በመሆኑ አገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በህብረት ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ የለም ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የሚከተለው አጀንዳ እሱ ከሚያነሳቸው ሰብዓዊ መብትና ራስን በራስ ከማስተዳደር አጀንዳዎች ጋር በፍጹም የሚገናኝ አይደለም ያሉት አቶ ሙስጠፌ ፤ እነዚህን አጀንዳዎች የሚያነሳቸው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማወናበድ እንጂ የእሱ ዓላማ አገርን ማፍረስ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የተናጠል የተኩስ አቁሙ ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍና ለአርሶ አደሩ እርሻ ሥራ ሲባል በመንግሥት የተደረገ ውሳኔ መሆኑን ልቡ እያወቀ ውሳንውን እንደ ፍርሐት በመቁጠር ተደፋፍሮ ክልሎችን ለማጥቃትና አገሪቱን ለማፍረስ እየሞከረ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ ክብርና ኀዘኔታ ቢኖረው ኖሮ በሌሎች ክልሎች ላይ ዳግመኛ ትንኮሳ ማሄድ የለበትም ነበር ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በአፋርና በአማራ ክልሎች ትንኮሳ ማካሄዱ አጀንዳው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነውም ብለዋል።
በመሆኑም አገር ለማፍረስ የሚንቀ ሳቀሰውን ይህንን ኃይል በህብረት ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌለ ማሳሰባቸውን ከኢፕድ ያገኘነው ዘገባ ያመለክታል።



