የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጽያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አድርጓል፡፡
ውይይቱ በቀጣይ በኢንቨስትመንት አካባቢዎች ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግስት ከኢንቨስተሮች ጋር በጋራ በመሆን ጥናቶችን በማካሄድና አዳዲስ ስልቶችን በማፈላለግ በዘላቂነት አብሮ መስራት በሚቻልበት መንገድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር የህግ የበላይነት ማስከበር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ፍሬ ዓለም ሺባባው መንግስት የተሻለች አገርን ለመገንባት ለውጪ ኢንቨስትመንት ክፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ለሰላምና ጸጥታ ችግሮችም መፍተሄ በማፈላለግ ኢንቨስተሮች ያለስጋት ወደ ስራ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ በፊት ኢንቨስተሮች ባቀረቡት የፀጥታ ስጋት ጥያቄ መሰረትም መንግስት በኢንቨስትመንት አካባቢዎች ለ 24 ሰዓታት ጥብቅ ክትትል ማድረጉ የተገለፀ ሲሆን ምርጫው በሰላም በመጠናቀቁን ኢንቨስተሮች የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ከኢንቨስትመንቶች በሚገኙባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ቀጣይነት ባለው መልኩ ከኢንቨስተሮች ጋር በመሆን ለመስራት መንግስት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ኢንቨስተሮች የስራ እንቅስቃሴያቸውን ለማህበረሰቡ ክፍት በማድረግ የባለቤትነት ስሜት መፍጠር እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል።
በውይይቱ ላይ የተካፈሉ ዓለማቀፍ ኢንቨስተሮችም ቀጣይነት ባለው መልኩ ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆን በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት መግለፃቸውን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አስታውቋል፡፡






