የደቡብ ብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም ህዉሀት በሽብር ተግባሩ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሊመኝና ሊሞክር ይችላል እንጂ በፍጹም ተግባራዊ ሊያደርግና ሊያሳካ አይችልም ሲል የገለፀ ሲሆን ክልሉ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃልም እንደሚከተለው ቀርቧል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከህወሀት የሀገር ክህደት ተግባራዊ እርምጃ በኋላ መንግስት ሲያካሂድ የቆየዉ የህግ ማስከበር ዘመቻ የተናጥል የተኩስ አቁም እርምጃ ሲወስድ ህዝቡ በጦር እንቅስቃሴ ሳይረበሽ የመኸር እርሻውን የሚያከናውንበት ሁኔታ እንዲፈጠርለት እና የሰብአዊ እርዳታና ድጋፍ አቅርቦ በነፃነት የሚከናወንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ነዉ፡፡
ይሁን እንጅ አሸባሪው ቡድን በመንግስት የተወሰደዉን የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ተጠቅሞ ከስህተቱ ከመማር ይልቅ ኢትዮጵያን የማፈራረስ የጋራ ዓላማ ካላቸው ሃይሎች ጋር በመተባበር ሀገራችንን ለማፍረስና ሉአላዊ ክብሯ እንዲደፈር እየሰራ ይገኛል፡፡
ይህ የሽብር ቡድን ለዚህ እኩይ አላማው፤ እድሜያቸዉ ያልደረሱ ህፃናትን፤ የሃይማኖት አባቶችን፤ ሴቶችን ጨምሮ በግዳጅ በጦርነት በመማገድ ለሃገራችን ብቻ ሳይሆን ለአለም አቀፍ ህግጋት ተፈጻሚነት ደንታ የሌለው ጨካኝ ቡድን መሆኑን በይፋ እያስመሰከረ ይገኛል፡፡
አሸባሪው ሕወሃት ኢትዮጵያን በበላይነት በመራበት ዓመታት ሁሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዳይቆሙ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል:: በብሔር፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖትና በተለያየ መነሻ ሲከፋፍልና ሲያጋጭ መቆየቱም መላው የክልላችችን ህዝብ የሚያውቀው እውነታ ነዉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን በመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብና ሀገራችን ላይ የከፈተዉን ጦርነት የሀገሪቱ ዉስን ክፈሎች ለማስመሰል በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳዉ ለማሞኘት ሲዳዳዉ ይደመጣል፡፡
ስለሆነም የክልላችን ህዝብና መንግስት የዚህ አሸባሪ ቡድን የሀገር ክህደት እኩይ ተግባር በድጋሚ አጥብቆ ያወግዛል::
በዚህ አሸባሪ ቡድን የተቃጣዉም ጥቃት በአንድ አካባቢ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ህልዉናና ሉአላዊነቷ ላይ መሆኑን መላዉ የክልላችን ህዝብ በሚገባ ይገነዘባል፡፡
ህዉሀት በሽብር ተግባሩ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሊመኝና ሊሞክር ይችላል እንጂ በፍጹም ተግባራዊ ሊያደርግና ሊያሳካ አይችልም:: ሀገራችን በልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረች፣ ዛሬም በሉአላዊነቷ የማይደራደር ትውልድ ያላት ስለመሆኗ ከዚሁ የሽብር ቡድን በላይ ምስክር አያሻውም፡፡ ይሁንና አሁንም ይህ የሽብር ቡድን ከድርጊቱ መመለስ እስካልቻለ ድርስ መንግስት በአሸባሪ ቡድኑ የሚወስደዉን እርምጃ የክልላችን መንግስትና ህዝብ እስከአሁን ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ አሁንም በሚፈለገው ሁሉ ድጋፉ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በመሆኑም መላዉ የክልላችን ህዝቦች ለሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ከምናደገው ድጋፍ ጎን ለጎን የአካባቢያችንን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ፣ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በትብብርና በቅርበት በመስራት፣ ለህዳሴ ግድባችን ድጋፋችንን በማጠናከር፣ አገራዊ ሃላፊነታችንን በንቃት እንድንወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
የደቡብ ብሄሮች: ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት
ሀዋሳ



