በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ከማዕረጋቸው በተጨማሪ “ጀግና” ተብለው እንዲጠሩና ማንኛውንም አገልግሎት ሲፈልጉ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) መወሰኑ ተገለፀ።
ጨፌው 14ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እውቅና መስጠት የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ አቅርበው ፀድቋል።
አፈ ጉባኤዋ በማብራሪያቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሲል ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈለ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፈፀመውን የአገር ሉዓላዊነት የመድፈር ወንጀል ሰራዊቱ በከፍተኛ ጀግንነትና መስዋእትነት ጭምር መቀልበሱን ጠቅሰዋል። “በዚህም ለአገር መከላከያ ሰራዊት እውቅና መስጠት አስፈልጓል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተጨማሪም የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በክልሉ ማንኛውንም አገልግሎት ሲፈልጉ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጨፌው ወስኗል።




