የሕዳሴ ግድቡን ቀጠና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ነን፡- የደቡብ፣ ሲዳማና ጋምቤላ ክልሎች ልዩ ኃይል አባላት

0
1092

ኢትዮጵያ ከልማት ጋር የተሳሰረችበትን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጠና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ግዳጃቸውን ለመወጣት ቁርጠኞች መሆናቸውን የደቡብ፣ ሲዳማ እና የጋምቤላ ክልሎች ልዩ ኃይል አመራርና አባላት ገለጹ።

አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው በመተከል ዞን የሕዳሴ ግድብ ቀጣና ግዳጅ ለመወጣት ለመጡ የክልሎቹ ልዩ ኃይል አመራርና አባላት የስራ ስምሪትና መመሪያ ተሰጥቷል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ፤ በተወሰደው የሠላም ማረጋጋት እርምጃ በቀጠናው ሠላም መስፈኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ሲፈጠር የነበረውን ሞትና መፈናቀል በማስቆም ታጥቀው ጫካ ገብተው ለነበሩ ታጣቂዎች የሠላም ተሃድሶ ስልጠና መስጠቱንና ከቀያቸው ተፈናቃዮችን ወደ የወረዳቸው መመለስ መቻሉንም አስረድተዋል።

ቀጣይ ግዳጆች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግና ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን ቀድሞ ማክሸፍ መሆኑን ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ መግለፃቸውን ነው ኢዜአ የዘገበው።

የልዩ ኃይል አባላቱ በየክልላቸው ያከናወኑትን የሠላምና ማረጋጋት ስራ በመተከል ዞን ለመድገም ግዳጅ ተቀብለው ወደ ቀጣናው በመምጣታቸውም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጠናው የሚገኘው የኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በሚገባ እንዲወጡም አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮ የልዩ ኃይል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮሚሽነር አለማየሁ ባውዲ “ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ ከልማት ጋር ቀለበት ያሰረችበትን የሕዳሴ ግድብ ቀጠና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የተገኘው እድል ያኮራል” ብለዋል።

የልዩ ኃይል አባላቱ የክልሎቻቸውን ሕዝብ በማሳተፍ በሠላምና ደህንነት ስራዎች ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮርዳክ ልዩ ኃይል አባላቱ የተቀበሉትን አገራዊ ተልዕኮ በሙሉ ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የክልሉ ልዩ ኃይል የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው የሚፈጽሟቸውን ትንኮሳዎች ሲያከሽፍ የቆየ ጀግና ኃይል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን በተሰለፈበት ቀጣና የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት በመወጣት የአገርን ሉዓላዊነትና የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የቀደመ ልምዱ እንደሚያግዘው አመላክተዋል።

የልዩ ኃይል አባላት በበኩላቸው በቀጣናው ማንኛውም ጸረ ሠላም ኃይል ለመፈጸም የሚያስበውን እኩይ ዓላማ ለመመከት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህነንትና ሠላም ለማስጠበቅ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የተሰጣቸው ግዳጅ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ያካተተ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸው በአሸናፊነት ለመውጣት እንደሚተጉ መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here