ባለፉት 10 ወራት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ህገወጥ ስራ ሲያከናውኑ በነበሩ 6መቶ 50 የደንብ አስከባሪዎች ላይ ከስራ እስከ ማገድ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ባዩ ሽጉጤ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በከተማዋ በደንብ ማስከበር ስራ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጭ የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ ደርሰንበታል ሲሉ ገልፀዋል።
ባለፉት 10 ወራት ህገወጥ ስራ ሲሰሩ በነበሩ 6መቶ 50 የደንብ አስከባሪ አባላት ላይ እስከ ስራ ማገድ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንም አስረድተዋል።
የደንብ አስከባሪዎች በከተማዋ የሚስተዋሉ ህገወጥ ስራዎችን ማጋለጥና መከላከል ሃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም ሁሉም የደንብ አስከባሪ ግን ኃላፊነቱን እንደማይወጣ ተነግሯል።
ሁሉም የደንብ አስከባሪ ማለት ባይቻልም በተለያዩ ወረዳዎች ኃላፊነቱን የማይወጣ እንዳለም ነው አቶ ባዩ የገለፁት።
በቀጣይ የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ ቢሮው የቁጥጥርና ክትትል ስራውን አጠናክሮ እንደሚያከናውንም ኃላፊው ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ከ 5 ሺህ በላይ የደንብ አስከባሪዎች ያሉ ሲሆን ቁጥሩን ከፍ በማድረግ ህገወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራ ቢሮው አስታውቋል።



